Fana: At a Speed of Life!

ከ25 በላይ ግለሰቦችን የማታለል ወንጀል ፈጽሟል የተባለ ግለሰብ ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ያለምንም ቅድመ ክፍያ ወደ ተለያዩ ሀገራት ለሚጓዙ ሰዎች ቪዛ እናስጨርሳለን የሚል ሃሰተኛ መረጃ በቲክቶክ በመልቀቅ እና ሃሰተኛ ቪዛ በማዘጋጀት ከ25 በላይ ሰዎች ላይ የማታለል ወንጀል ፈጽሟል የተባለ ግለሰብ ክስ ተመሰረተበት፡፡

ተጠርጣሪው ከ50 እስከ 600 ሺህ ብር ከእያንዳንዳቸው መቀበሉንም በፖሊስ መረጋገጡ ተገልጿል፡፡

ግለሰቡ የወንጀል ድርጊቱን ፈጽሟል የተባለው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ቆሬ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደሆነም ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ወንጀል መርማሪ ረዳት ኢንስፔክተር ጌታ ደረሰ እንደገለፁት÷ ግለሰቡ ባሰራጨው የሃሰት መረጃ ወደ ካናዳ ለመጓዝ ፍላጎት አሳይተው ከተጠርጣሪው ጋር የተገናኙ ሰዎች አብዛኞቹ የወንጀሉ ሰለባ ሆነዋል።

ተጠርጣሪው ያለምንም ቅድመ ክፍያ የቪዛ ፕሮሰስ እጨርሳለሁ ቢልም ጉዳይ እንዲያስፈፅምላቸው የተለያየ ቦታ እየቀያየረ በቀጠሮ ሲያገኛቸው ከነበሩ ባለጉዳዮች ቪዛ እንዳለቀላቸው እየነገረ እና ሌሎች ምክንያቶችን እየሰጠ ከእያንዳንዳቸው ገንዘብ መቀበሉ ተጠቅሷል፡፡

ተጠርጣሪው ተበዳዮች እንደተጠራጠሩት ሲያውቅ ቤት ተከራይቶ የማታለል ወንጀሉን ሲፈፅም ከነበረበት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ቆሬ አካባቢ በመሸሽ ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ቡልቡላ ማርያም ማዞሪያ አካባቢ ሌላ ቤት ተከራይቶ ወንጀሉን መፈፀም እንደቀጠለ እና ፖሊስ ባደረገው ክትትል እንደተያዘ ተናግረዋል፡፡

ረዳት ኢንስፔክተር ጌታ ደረሰ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በተደረገ ፍተሻ ሀሰተኛ ሰነዶች እና ሰነዶቹን ለማዘጋጀት ሲጠቀምባቸው የነበሩ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ተገኝተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.