Fana: At a Speed of Life!

የመጋዘን ኃላፊው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ መድሐኒት በመሰወር ሙስና ወንጀል ክስ ቀረበበት

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የመድሐኒት አቅራቢ ድርጅት የመጋዘን ኃላፊው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ መድሐኒት በመሰወር የሙስና ወንጀል ክስ ቀረበበት።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ጀነራል በኢትዮጵያ መድሐኒት አቅራቢ አገልግሎት የመጋዘን ኃላፊ በነበረው እና በተመሳሳይ ወንጀል ተከሶ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኘው ሚካኤል ዘዉገ ተሰማ ላይ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 31 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፏል በማለት ክስ አቅርቦበታል።

በቀረበበት ክስ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው፤ ተከሳሹ በኢትዮጵያ መድሐኒት አቅራቢ አገልግሎት ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኙ የሁለት መጋዘኖች ኃላፊ ሆኖ በሚያስተዳድርበት ወቅት የኢትዮጵያ መድሐኒት አቅራቢ አገልግሎት አንቲ አርኤችኦ (ዲ) ኢሚዩን ግሎቡሊን (Anti-Rho (D) Immune Globulin 300 Mg in 2ml Vial- Injection) መድሐኒት መጠኑ በብልቃጥ 46 ሺህ 560 የሆነ ከበሀራት ሰሩም እና ቫሲን ኤልቲዲ (Bharat Serum and Vaccine LTD) ከተባለ አቅራቢ በግዥ ትዕዛዝ ከዉጭ ሀገር ያስመጣውን መድሐኒት መጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም ፈርሞ ከትራንዚተር ተረክቧል።

ከዚህ በኋላ መድሐኒቱን ወደ ሌላ “ሜይን 3″ወደ ተሰኘ መጋዘን አብሮ ገቢ ካደረገ በኋላ ከተረከበው አጠቃላይ 46 ሺህ 560 ብልቃጥ ውስጥ አጠቃላይ የዋጋ ግምቱ 1 ሚሊየን 114 ሺህ 857 ብር ከ87 ሳንቲም የሚያወጣ 900 ብልቃጥ መድሐኒት ሳያስረክብ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ያደረገ ወይም የሰወረ መሆኑ ተጠቅሶ በከባድ የእምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል ተከሷል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ክሱን ለመመልከት ለመጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.