Fana: At a Speed of Life!

የሪፐብሊኩ ጥበቃ ሃይል ያሰለጠናቸውን የልዩ ሃይል አባላት አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሪፐብሊኩ ጥበቃ ሃይል ያሰለጠናቸውን የልዩ ሃይል አባላት አስመርቋል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የሪፐብሊኩ ጥበቃ ሃይል ዋና አዛዥ ሜ/ጄ አብድሮ ከድር፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል፡

ሜ/ጄ አብድሮ ከድር እንዳሉት÷የሪፐብሊኩ ጥበቃ ሃይል የተቋቋመበትን ተልዕኮ በብቃት መፈፀም እንዲችል ታሳቢ ያደረገ አቅም ፈጣሪ ስልጠናዎችን በመውሰድ ሞራላዊ ብቃቱን እያሳደገ በዘመናዊ ትጥቆች እራሱን እያደራጀ ነው፡፡

በተለያየ ጊዜ ከዘመናዊ ልዩ ጥበቃ ጀምሮ እስከ መደበኛ ጦርነትና የሽምቅ ውጊያ በመሳተፍ ያሥመዘገባቸው አመርቂ ውጤቶች ሁለገብ የሆነ የተልዕኮ አፈፃፀም ብቃቱን እንደሚያረጋግጡም ነው የተናገሩት፡፡

ያልተሞረደ ሰይፍ የመቁረጥ አቅሙን እንደሚያጣ ሁሉ በየጊዜው በስልጠና ራሱን እያበቃ የማይሄድ ወታደር ግዳጅ የመወጣት እና የማሸነፍ አቅም አይኖረውም ሲሉ የሥልጠናን አሥፈላጊነት ገልፀዋል፡፡

ተመራቂዎችይህ የስልጠና መጨረሻ ምዕራፍ እንዳልሆነ በመገንዘብ በማንኛውም ጊዜ ራሳቸውን ለተሻለ ተልዕኮ እንዲያዘጋጁ ማሰሰባቸውንም የመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡

ከሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው እንደገለጹት ÷ የሪፐብሊኩ ጥበቃ ሃይል ሀገራችን ችግር በገጠማት ጊዜ በየትኛውም ግንባር ተሰልፎ በልዩ ሁኔታ ጀግንነት እየፈፀመ ያለ ክፍል ነው፡፡

በአዲስ አበባ በማንኛውም የፀጥታ ሁኔታ ውስጥ በተለይም ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ የከተማዋን ሰላም አስጠብቋልም ነው ያሉት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.