Fana: At a Speed of Life!

ረመዳንን ስንቀበል ለፍቅር ቅድሚያ መስጠት ይገባል- የእስልምና ሐይማኖት መምህራን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ረመዳንን ስንቀበል እርቅና ፍቅርን የማውረድ ሥራን በማስቀደም ሊሆን ይገባል ሲሉ የእስልምና ሐይማኖት መምህራን አስገነዘቡ፡፡

የረመዳን ወር ለጥፋቶቻችን ምኅረት የምናገኝበት፣ ጉድለቶቻችንን የምናራግፍበት እና አላህን የምንለምንበት ነው ሲሉ ሼህ መሐመድ ሀሚድ ገልጸዋል፡፡

ወሩ አማኙ ረሃብና ጥማትን ተገንዝቦ ለተቸገሩት ሁሉ የሚራራበት ሰደቃ የሚያበዛበት መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ዓይን ክፉ ነገር ከማየት፣ ጆሮ ሃሜት ከመስማት አንደበትም ክፉ ከመናገር የሚርቅበት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ኡስታዝ አብደላ ከድር (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የረመዳን ወርን ለመቀበል የሚደረግ ዝግጅት ከቁሳዊ ዝግጅት ከፍ ያለና ወደ አላህ መመለስን የሚያስቀድም መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ረመዳን ከመግባቱ በፊት አማኙ ከቁሳዊ ዝግጅቶች አስቀድሞ ከሰው ልጅና ከፍጥረታት ጋር ያለውን መልካም መስተጋብር ማስተካከል እና ለእርቅና ፍቅር ቅድሚያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

አማኙም በመደጋገፍ፣ ለሀገር ሰላምና አንድነት በመጸለይ ወሩን ማሳለፍ እንዳለበት መምህራኑ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል፡፡

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.