Fana: At a Speed of Life!

ጾምና የጤና በረከቶች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የዐቢይ ጾም እንዲሁም በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ደግሞ የረመዳን ጾም በዛሬው ዕለት ተጀምሯል፡፡

በሁለቱም እምነቱ ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት ከሚሰጣቸው የጾም ወቅቶች ጋር ተያይዞም የጾም ጠቀሜታዎች ለማንሳት ወደናል።

ጾም በበርካታ ህዝቦች የሚከወን እና በተለይም በሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች ላይ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ተግባር ነው።

ከዚህ ቀደም በኒው ሜዲካል ጆርናል መጽሄት ላይ የወጣው የጥናት ውጤት እንደሚያሳየው፤ በቀን ከ16 እስከ 18 ሰዓት ምግብ ሳይመገቡ ማሳለፍ የተለያዩ የጤና በረከቶችን ያስገኛል።

በመሆኑም ከጾም የሚገኙ የጤና ጠቀሜታዎች፡-

• በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ለመቆጣጠር፣

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ጾም በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን በተሻለ መንገድ ለመቆጣጠርና በተለይም የስኳር በሽታ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ጠቃሚ መሆኑ ነው የተመላከተው።

• እብጠትን በመከላከል ሰዎች ጤናማ እንዲሆኑ ያስችላል፣

ከዚህ ጋር ተያይዞ የወጡ ጥናቶች በጾም ወቅት ሰውነት የሚያገኘው የካሎሪ መጠን ከመቀነሱ ጋር ተያይዞ ሰውነት ላይ የሚከሰት እብጠት እንደሚቀንስ ያሳያሉ።

በአንድ ጥናት ላይ የተሳተፉ 50 ሰዎች ለአንድ ወር እንዲጾሙ የተደረገ ሲሆን በዚህም ከፍ ባለሁኔታ የእብጠት መጠን እንደቀነሰላቸው ተጠቁሟል።

ሌላኛው ጥናትም ሰዎች ለ12 ሰዓታት ሲፆሙ ተመሳሳይ ውጤት እንደተመለከቱ ተነግሯል።

• የደም ግፊትን እና የኮሌስትሮል መጠንን ለመከላከል፣

• ከፍተኛ የክብደት መጠንን ለመቀነስ፣

ከመጠን በላይ ለሆነ ውፍረት የተጋለጡ ሰዎች በተደጋጋሚ እንዲፆሙ ተደርጎ የሰውነት ክብደታቸው መቀነሱ ተጠቅሷል።

የሰውነት ክብደታቸው መቀነሱ ደግሞ የደም ግፊታቸውና የኮሌስትሮል መጠናቸው እንዲቀንስ ረድቷቸዋል፤ ይህ ደግሞ ከልክ በላይ በሆነ ውፍረት ሊከሰት የሚችለው የልብ ጤንነት ችግርን መቅረፍ ያስችላልም ነው የተባለው።

• ፆም የአዕምሮ የመስራት አቅምን ያፋጥናል፣ ከነርቭ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን ይከላከላል፣ የሰውነት ክብደትን ለመቀነስ ይረዳል፣ ካንሰርን ለመከላከል እና ለምግብ መፈጨትና ለስርአት ምግብ መንሸራሸርን ለማፋጠን እንደሚረዳ የሄልዝ ኦንላይን መረጃ ያመላክታል፡፡

እንዲሁም ክብደት ለመቀነስ እና አጥንትን ለማጠናከር ወሳኝ የሆነውን ሆርሞን እድገት ለመጨመር እንደሚጠቅምም ነው የተጠቆመው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.