Fana: At a Speed of Life!

በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ የለሚኩራ ክ/ከተማ የቀድሞ 3 ሠራተኞች በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ታዘዘ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የለሚኩራ ክፍለ ከተማ የመሬት ዝግጅትና ማስተላለፍ ዘርፍ አስተባባሪና የሊዝ ውል ባለሙያ የነበሩ ሦስት ተከሳሾች በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት ትዕዛዝ ሰጠ።

ተከሳሾቹ÷ 1ኛ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የመሬት አሥተዳደር ጽ/ቤት የመሬት ዝግጅትና ማስተላለፍ ዘርፍ ሥራዎች የቀድሞ አስተባባሪ አቶ ዘውዱ ኤርጆቦ፣ 2ኛ በዚሁ ክፍለ ከተማ የቦታ ማስከበርና ሊዝ ክትትል ቡድን ተወካይ አስተባባሪ የነበሩት አቶ እንግዳ ሙሉነህ እና የሊዝ ውል የቀድሞ ባለሙያ አቶ ፍፁም ደምሴ ናቸው።

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ጀነራል÷ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና ለ እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት የማይገባ ጥቅም መቀበል ከባድ ሙስና ወንጀል ከሷቸዋል፡፡

በዚህም አቾንቴን ትሬዲንግ ኃ.የተ.የግል ማኅበር የይዞታ ስፋቱ 1 ሺህ 22 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ የሊዝ ጨረታ አሸንፎ በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ ወደ ግንባታ ያልገባበትን ምክንያት ጠቅሶ የሊዝ ውሉ እንዲራዘምለት በወኪሉ አማካኝነት ነሐሴ 3 ቀን 2015 ዓ.ም የአገልግሎት ጥያቄ ሲያቀርብ “የሊዝ ውሉ እንዲራዘምለት ከፈለገ ለሥራው ማከናወኛ ለሰባት ሠራተኞች የሚከፋፈል ሦስት ሚሊየን ብር ይክፈል” የሚል ጥቅም ተከሳሾቹ መጠየቃቸው በክሱ ተመላክቷል፡፡

በ2ኛ እና በ3ኛ ተከሳሾች አማካኝነትም የገንዘብ መጠን ሲደራደሩ ከቆዩ በኋላ÷ 1 ሚሊየን 500 ሺህ ብር ለመቀበል በመስማማት፣ 1ኛ ተከሳሽ ደግሞ ጉዳዩን ለክፍለ ከተማው ፕሮሰስ ካውንስል አስቀርቦ ለማስወሰን የሊዝ ውል እንዲሻሻል ለማድረግ በመስማማትና ካውንስሉ እንዲወስን በማድረግ፣ 3ኛ ተከሳሽም ተወስኖ ያለቀለት መሆኑን ለግል ተበዳይ በመግለጽና በእህቱ ስም በንግድ ባንክ በተከፈተ አካውት ገንዘቡን አስገብቶ ወረቀቱን እንዲወስድ እንደተጠየቀ በክሱ ተገልጿል፡፡

የግል ተበዳይ በተጠየቀው መሰረትም ታኅሣስ 22 ቀን 2016 ዓ.ም 1 ሚሊየን 200 ሺህ ብር መክፈሉንና በተጨማሪም የቀድሞ መሬት አሥተዳደር ሕንጻ ላይ በሚገኝ አንድ ካፌ ውስጥ 3ኛ ተከሳሽ 200 ሺህ ብር ተቀብሎ ሊሄድ ሲል በተደረገ ክትትል እጅ ከፍንጅ መያዙን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡

በዚሁ መሠረትም ሁሉም ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የማይገባ ጥቅም መቀበል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

ለተከሳሾቹ ክሱ እንዲደርስ ከተደረገና በንባብ ከተሰማ በኋላ ክሱ እንዲሻሻል የክስ መቃወሚያ በጽሑፍ ማቅረባቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ክሱ ሊሻሻል የሚችልበት የሕግ መሰረት አለመኖሩን ጠቅሶ መልስ ሰጥቶ ነበር፡፡

ዛሬ በዋለው የችሎት ቀጠሮም ተከሳሾቹ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ የጠቀሱት ፍሬ ነገር የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ የሚመረመር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን÷ የክስ መቃወሚያቸውም ውድቅ ተደርጓል።

ተከሳሾቹም በክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት እንዳልፈጸሙ በመግለጽ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን ምስክሮች ቃል እንዲሰማለት መጠየቁን ተከትሎም ፍርድ ቤቱ ለዐቃቤ ሕግ ምስክሮች መጥሪያ እንዲደርስ በማዘዝ የምስክሮችን ቃል ለመስማት ለመጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ተከሳሾቹም በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ፤ የለሚ ኩራ ፖሊስም ተከሳሾቹን ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.