Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን እሴት ለጎብኚዎች የሚያስተዋውቅ መርሐ ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን እምቅ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ እሴት ለአሜሪካውያን ጎብኚዎች የሚያስተዋውቅ መርሐ ግብር በዋሽንግተን ዲሲ ተካሂዷል፡፡

የመርሐ ግብሩ ዓላማ ኢትዮጵያ በቱሪዝም መስክ ያላትን መስህብ በአሜሪካ ለሚገኙ የውጭ ዜጎች ማስተዋወቅና ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በመርሐ ግብሩ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ዘላለም ብርሃን ÷በኢትዮጵያ የሉሲ ወይም ድንቅነሽ ቅሪተ አካል፣ የጥንት ስልጣኔዎች፣ የዘመን አቆጣጠር፣ ቡና ፣ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች እና ሌሎች መስህቦች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በአፋር ክልል የሚገኘው እሳተ ጎሞራ፣ የኮንሶ የባህል ገጽታ፣ የአጥቢ እንስሳትና አእዋፍ ሀብት እንዲሁም የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ምልክት የሆነው የዓድዋ ድልን ጨምሮ ጥንታዊት የአፍሪካም አገር መሆኗን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተወዳጅ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች እንዳሏት በመግለጽ በቱሪዝም ያላትን ሀብት ሁሉም እንዲጎበኝ እና የውጭ ባለሃብቶችም በዘርፉ ላይ መዋዕለንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅረበዋል።

የዝግጅቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የበርካታ ባህሎች እና የባህል ምግቦች መገኛ መሆኗን ጠቅሰው÷ መድረኩም ቅርሶቿን ለማወቅና ለመረዳት ጥሩ አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

በቀጣይም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ጉብኝት ማድረግ እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.