Fana: At a Speed of Life!

ከተለያዩ ከተሞች የተወጣጡ ከንቲባዎች በመዲናዋ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች የተወጣጡ ከንቲባዎች በአዲስ አበባ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር እና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ በጉብኝቱ ወቅት÷አዲስ አበባ ላይ  በተለያዩ  ዘርፎችለውጥ ማምጣት የቻልነው የአስተሳሰብ ለውጥ በማድረጋችን ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከተሞች ከፕላን ውጪ ሲገነቡ ችላ መባላቸው ዛሬ ላይ በከተማ መዋቅራዊ ፕላን መሰረት የልማት ሥራዎችን ለመተግበር መሰናክል እንደሆኑ እንስተዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁን ላይ ተመሳሳይ ስህተት እንዳይፈጠር የከተማ አስተዳደሩ አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ እና አበባ ለማድረግ በከተማዋ ስታንዳርድ ልክ ፕሮጀክቶችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አለምጸሃይ ጳውሎስ በበኩላቸው÷የኮሪደር ልማት ስራዎችን እንደ ሀገር በማስፋት ከተሞችን ውብ፣ ጽዱ እና ለመኖር ምቹ ማድረግ አለብን ብለዋል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ÷ቆራጥነትንና የምንናገረውን በተግባር መለወጥን ከአዲስ አበባ ተሞክሮ መውሰድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ለህዝብ የተገባውን ቃል ለመተግበር የህዝቡን ችግር የሚቀርፉ ሥራዎች ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በጉብኝቱ የተሳተፉ ከንቲባዎቹ÷ የአዲስ አበባ ከተማ ፕሮጀክት ጀምሮ የማጠናቀቅ ፣የአመራር ቁርጠኝነት እና ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ የመስራት ትልቅ ልምድ የሚቀሰምባት ከተማ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ጨምሮ የከተማዋን ገፅታ የሚቀይሩ እና የነዋሪውን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች ናቸው ማለታቸውንም የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.