Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ ቅሬታዎችን መርምሮ ተገቢ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ እየተሰሙ ያሉ ቅሬታዎችን መርምሮ ተገቢ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡

ዓየር መንገዱ ሰሞኑን በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከመንገደኞች አገልግሎት አሠጣጥ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ቅሬታዎች እየተነሱ መሆኑን መገንዘቡንም ገልጿል።

እንዲሁም ከደንበኞቹ ለሚቀርቡ ቅሬታዎች እና አስተያየቶች ትኩረት የሚሠጥ መሆኑን በመግለጽ ሂደቱን በጥሞና ሲከታተል መቆየቱንም አስታውሷል፡፡

በመሆኑም እየተሰሙ ያሉ ቅሬታዎችን መርምሮ መፍትሄ ለመስጠት ዓየር መንገዱ በአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ አገልግሎት ከሚሰጡ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ቅሬታዎችን የማጣራት ስራ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በዚህም በማጣራቱ በሚገኙ ውጤቶች ላይ በመመርኮዝ ተገቢው የማስተካከያ እርምጃ በፍጥነት እንዲወሠድ ይደረጋል ነው ያለው፡፡

ዓየር መንገዱ ለደንበኞቹ ቀልጣፋ እና ምቹ አገልግሎት መስጠት ዋነኛ ተግባሩ መሆኑን አስታውሶ፤ አሁንም የደንበኞቹን ጥቆማ ተቀብሎ አስፈላጊውን ማስተካከያ የማድረግ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የዓየር መንገዱ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.