Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ የግሉ ዘርፍ አረንጓዴ ኢንቨስትመንቶች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የግሉ ዘርፍ በአረንጓዴ ኢንቨስትመንቶች ላይ ይበልጥ ትኩረት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡

6ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በሩዋንዳ ኪጋሊ እየተካሄደ ሲሆን ፥ የግሉ ዘርፍ አረንጓዴ ኢንቨስትመንቶችን መጠቀም በሚችልበት ሁኔታ ትኩረት ማድረጉ ተመላክቷል፡፡

ጉባዔው በዓለም አቀፍ የፋይናንስ አለመረጋጋት ውስጥ የግሉ ዘርፍ አየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉ ስትራቴጂዎችን ለማሳደግ አረንጓዴ ኢንቨስትመንቶችን እንዲያጠናክር አሳስቧል።

የሩዋንዳ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ክላውዲን ኡዌራ እንዳሉት ፥ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቅረፍ መሰል ኢንቨስትመንቶች መጠናከር አለባቸው፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ የተላመዱ ስትራቴጂዎችን ከሰፊ ሀገራዊ ፖሊሲዎችና የዕቅድ ሒደቶች ጋር ማቀናጀት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጉባዔው በአየር ንብረት ፋይናንስ ፍላጎት እና አቅርቦት መካከል ያለውን ልዩነት ለማስተካከል ትብብርና የጋራ ጥረቶች እንዲደረጉ ያስችላልም ብለዋል።

የጉባዔው ተሳታፊዎች ፥ የአየር ንብረት ለውጥን የመላመድ እና የመቋቋም ጥረቶችን ለማጎልበትና በአፍሪካ ሀገራት ሊተገበሩ የሚችሉ ፕሮግራሞችን በመፍጠር ላይ የግሉ ዘርፍ ያለውን ወሳኝ ሚና አጽንኦት ሰጥተዋል።

ጉባዔው የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችሉ ኢንቨስትመንቶችን ለማቀድ፣ ለመንደፍ እና ተግባራዊ ለማድረግ የተቋማትን እና የግሉን ዘርፍ አቅም ለማጠናከር ያለመ ነው መባሉን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.