ሶስት ሀገር በቀል ኩባንያዎች የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት አገልግሎት ፈቃድ አገኙ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሶስት ሀገር በቀል ኩባንያዎች መልቲ ሞዳል ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን ፈቃድ አገኙ።
ድርጅቶቹ የብቃት ማረጋገጫ እውቅና የምስክር ወረቀት ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እጅ ተቀብለዋል።
ፓናፍሪክ ግልባል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ ጥቁር አባይና ኮስሞስ መልቲ ሞዳል ሼር ካምፓኒ የመወዳደሪያ መስፈርቱን አሟልተው የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ የተሰጣቸው ድርጅቶች ናቸው።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንደተናገሩት÷ የኢትዮጵያን ሎጂስቲክስ አገልግሎት ተወዳዳሪ ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ድርሻ ከፍተኛ ነው።
የግል ድርጅቶች የሎጂስቲክስ አገልግሎት እንዲሰጡ የግሉን ዘርፍ የሚያሳትፍ መመሪያ መዘጋጀቱን ጠቁመው÷ በመመሪያው መሰረት ለግል ትራንስፖርት ሰጪ ድርጅቶች ፈቃድ መሰጠት መጀመሩን ገልፀዋል።
ዕውቅና እና ፈቃድ የተሰጣቸው ድርጅቶችም ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡