Fana: At a Speed of Life!

አቶ አህመድ ሺዴ መንግስት ከልማት አጋሮች ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ፣ ሰላም ግንባታና የተፈጥሮ አደጋዎችን በመቋቋም ላይ ያተኮረ ከፍተኛ የመንግስትና የልማት አጋሮች የጋራ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች፣ የልማት አጋር ድርጅቶች ሃላፊዎች፣ አምባሳደሮችና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡

ውይይቱ ለማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶች እልባት መስጠት፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች መቋቋምና ሰላምን ማጎልበትና ማስፈን በሚሉ ወቅታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ÷ መንግስት ከልማት አጋሮች ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ርእሰ ጉዳዮች ላይ ከልማት አጋሮች የሚገኘውን ገንቢ ሀሳብ፣ አስተያየትና ተሞክሮ መንግስት በአዎንታዊ መልኩ እንደሚቀበል አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ልማት የምታስመዘግበው ውጤት የአፍሪካ ቀንድን ለማረጋጋት አስተዋጽዖ ያለውና እንደ ቀጠናዊ ውጤት የሚቆጠር እንደሆነ ማንሳታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

መንግስት ከአጋሮች ጋር በትብብር የሚሰራውን ማክሮ ኢኮኖሚውን በዘላቂነት የማረጋጋት፣ ተቋማትን የማጠናከር፣ ሲቪል ሰርቪሱን የማዘመን፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ የማድረግና ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማቶችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በመድረኩ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በሀገሪቱ ልማትና ማክሮ ኢኮኖሚ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የልማት አጋሮች ተወካዮችና አምባሳደሮች ምክረ ሀሳብና አስተያየታቸውን ከማቅረባቸውም በላይ ከመንግስት ጋር በኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ላይ በትብብር እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.