ከ600 ሺህ የሚበልጡ ዘመናዊ ቀፎዎችን ለአርሶ አደሩ ማድረስ ተችሏል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ እስካሁን ከ600 ሺህ የሚበልጡ ዘመናዊ ቀፎዎችን ለአርሶ እና አርብቶ አደሩ ማድረስ እንደተቻለ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ የለውጡ መንግስት ዓላማ የበለፀገች ሀገር እውን ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
ግቡን ለማሳካትም በዓለም አቀፋዊነት እና ተወዳዳሪነት የሃሳብ ማዕቀፍ የተቃኘ የኢኮኖሚያዊ እይታን የሚከተል ይሆናል ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
በዚህም በግብርናው ዘርፍ፣ የግብርና ሥነ-ምህዳር አቅምን ከግምት ያስገቡ 27 የሚሆኑ ኢኒሼቲቮች በመተግበር ላይ ይገኛሉም ብለዋል።
ከእነዚህ መካከል በ2013 ዓ.ም በጅማ ከተማ የታወጀው “የጅማ አዋጅ” አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ÷ አዋጁ “ኦሮሚያን የማር ባህር እናደርጋለን” በሚል መሪ ሃሳብ የተያዘ የማር ልማት ኢኒሼቲቭ ነበር ነው ያሉት፡፡
ኢኒሼቲቩ ዘመናዊ ቀፎና ሳይንሳዊ የማነብ እውቀት ማስፋፋትን ያለመ ሲሆን ÷ እስካሁን በ15 ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 175 ወረዳዎች ማስፋፋት መቻሉንም ነው የተናገሩት፡፡
በ2015 ዓ/ም፣ 345 ሺህ ዘመናዊ ቀፎዎችን ለአርሶ እና አርብቶ አደሮች በማቅረብ 86 ሺህ ቶን ማር ማምረት ተችሎ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
በዚህ ዓመትም 1 ሚሊየን ዘመናዊ ቀፎዎችን 200 ሺህ ለሚበልጡ አርሶ/አርብቶ አደሮች በማከፋፈል 114 ሺህ ቶን ማር እና 7 ሺህ ቶን ሰም ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ነው ያመላከቱት፡፡
በእስካሁኑ አፈፃፀም ከ600 ሺህ የሚበልጡ ዘመናዊ ቀፎዎችን ለአርሶ/አርብቶ አደሩ ማድረስ የተቻለ ሲሆን ፥ በቀሪው ጊዜም የዓመቱን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል፡፡
ከመነሻው እንደታሰበው ፥ ዓለም አቀፋዊነትና ተወዳዳሪነት በሚሉ የሃሳብ ማዕቀፎች የተቃኘው የማር ልማት ኢኒሼቲቭ፣ ክልሉ ለውጭ ገበያ የሚያቀርባቸውን ምርቶች ብዝሃነትና መጠን በማሳደግ ላይ ይገኛልም ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡