Fana: At a Speed of Life!

አቶ አረጋ ከበደ የማዳበሪያ አቅርቦትን በጥንቃቄ ማሰራጨት እንደሚገባ አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) የማዳበሪያ አቅርቦትን በጥንቃቄ ማሰራጨት እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ የስምንት ወራት የሥራ አፈጻጸምና የቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት ያካሄደ ሲሆን ፥ በመድረኩ አቶ አረጋ ከበደን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በዚሁ ወቅት ÷ የማዳበሪያ አቅርቦትን በጥንቃቄ ማሰራጨት እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡

ካለው ማደበሪያ አንጻር የተሰራጨው ማደበሪያ ብዙ አለመሆኑን በመግለጽ የማዳበሪያ አቅርቦት ልዩ ትኩረት ሊሰጥበት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳሕሉ (ዶ/ር) ÷ ክልሉ ከገባበት ችግር ለመውጣት ምርት እና ምርታማነትን መጨመር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ወደ ክልሉ የሚገባውን ማዳበሪያ በፍጥነት ማሰራጨት እንደሚገባ በመግለጽ በግብርናው ዘርፍ የሥራ እድል መፍጠርን ታሳቢ በማድረግ በትኩረት እንዲሠራም ነው ያሳሰቡት፡፡

በክልሉ በተፈጠረው ግጭት የግብርናው ዘርፍ ጉዳት እንደደረሰበት ጠቅሰው ÷ በተፈጠረው ችግር በርካታ ሥራዎች ወደኋላ መቅረታቸውንም አንስተዋል፡፡

አሁን ላይ የሰላም ሁኔታው እየተሻሻለ ነው ያሉት ኃላፊው ÷ ከሰላም ሥራው ጎን ለጎን የልማት ሥራዎችን መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡

በመኸር ወቅት 5 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማረስ እንደታሰበም ገልጸው፥ በአማራ ክልል 3 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ መግባቱንም ነው የገለጹት፡፡

የእቅዱ 45 በመቶ የሚሆነው ማዳበሪያ እየገባ መሆኑን ጠቅሰው ÷ የቀረበውን ወደ አርሶ አደሮች ማሰራጨት ላይ ሥራዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡

አርሶ አደሮች ራሳቸውን እያደራጁ ማደበሪያ እንዳይዘረፍ የማድረግ ሥራ እንዲሠሩም ጥሪ ማቅረባቸውን የዘገበው አሚኮ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.