በመዲናዋ 435 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለመምህራን በዕጣ ተላለፉ
ከንቲባዋ እንደገለጹት፤ ከዚህ በፊት ለመምህራን ተላልፈው ከነበሩ 5 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ውል ሳይፈጸምባቸው የቆዩ 435 ቤቶችን በማጣራት ተለይተው ዛሬ በዕጣ ለቤት እድለኞቹ ተላልፈዋል።
ያለንን ውስን ሃብት በግልፀኝነትና በፍትሃዊነት በተገቢ ሁኔታ ለህዝባችን እንዲደርስ እያደረግን መስራታችንን እንቀጥላለን ሲሉም አረጋግጠዋል።
በዕጣው 30 ሺህ መምህራን መካከተታቸው የተገለጸ ሲሆን÷ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹም የመምህራንን ተልዕኮ ለማሳካት ብሎም ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫናዎችን ለማቃለል እንደሚያግዙ ተጠቅሷል፡፡
በመምህርነት ሙያ እስከ ዘጠኝ ዓመት ላገለገሉ መምህራን 81 ቤቶች፣ ከ10 እስከ 20 ዓመት ላገለገሉ 83 ቤቶች፣ ከ21 እስከ 34 ዓመት ላገለገሉ 91 ቤቶች እንዲሁም ከ35 ዓመት በላይ ላገለገሉ መምህራን 82 ቤቶች በዕጣው ተካትተዋል።
በተጨማሪም ለአካል ጉዳተኞች 48 እና ለሴቶች ደግሞ 50 ቤቶች በዕጣው ተካትተዋል፡፡
የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓቱም በቴክኖሎጂ የተደገፈና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ሲስተም የታገዘ ነው ተብሏል፡፡
በታሪኩ ወ/ሰንበት