Fana: At a Speed of Life!

የጎጃም ኮማንድ ፖስት ቀጣይ ግዳጅ ወረዳና ቀበሌን ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት – ሌ/ጄ መሐመድ ተሰማ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎጃም ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ እና የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌ/ጄ መሐመድ ተሰማ ከሁሉም የጎጃም ዞኖች ከተወጣጡ ከ400 በላይ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በመድረኩ በአማራ ክልል ኮማንድ ፖስት ደረጃ የተገመገመውን የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ ወደ ጎጃም ኮማንድ ፖስት በማውረድ በአመራሮቹ በስፋት መታየቱ ተጠቁሟል ።

ከሁኔታው ግምገማ በመነሳትም የቀጣይ ተግባራቶች ምን እንደሆኑ የጋራ ግንዛቤ መያዙ ነው የተገለጸው፡፡

ሌ/ጄ መሐመድ ተሰማ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ÷ የጎጃም ኮማንድ ፖስት ቀጣይ ግዳጅ ገጠርን ፣ ወረዳን እና ቀበሌን ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት ።

በአማራ ክልል የግብርና ሥራ እንዲካሔድ ፣ የትምህርት ፣ የጤና ፣ የንግድ ፣ የቱሪዝም እና ሌሎች አገልግሎቶች እንዲከናወኑ ሰላም መስፈን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ኮማንድ ፖስቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዕዝ የተሰጠውን ግዳጅ መፈጸም ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ጽንፈኛውን በመምታት የሰው ሃይሉ እንዲመናመን አድርጓልም ነው ያሉት፡፡

የሎጀስቲክስ አቅሙ እና ከደጋፊዎቹ የሚያገኘው ድጋፍም እንዲነጥፍበት ተደርጓል ፤ ከህዝብ እንዲነጠል የሚያደርጉ ስራዎችም ውጤታማ ሆነዋል ሲሉም ተናግረዋል።

በየዱሩ፣ በከተማ እና በየመንደሩ ተደብቀው የህዝብን ሰላም የሚነሱትን በማፅዳት ወደ ህግ የማቅረብ ግዳጃችንን መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል ።

በምክክር መድረኩ የፌዴራል ፣ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የኮማንድ ፖስቱ ጄኔራል መኮንኖች መሳተፋቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.