Fana: At a Speed of Life!

በአማራና ትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎች ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በአፋጣኝ እንዲፈቱ ስምምነት ላይ ተደረሰ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራና ትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎች ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በአፋጣኝና በዘላቂነት ሊፈታ እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደረሰ።

በአማራና ትግራይ ክልሎች መካከል የሚገኙና የወሰን ይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውን አካባቢዎች በህገ መንግስቱ እና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ መሰረት በዘላቂነት እልባት ለመስጠት በብሔራዊ ደረጃ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሲሠራ ቆይቷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የሁለቱ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተሳታፊዎች በተገኙበት የብሔራዊ ኮሚቴው አፈፃፀሙ ተገምግሟል።

የተፈፀሙና ሊፈፀሙ ሲገባቸው የዘገዩ ጉዳዮች ተነስተው ግምገማ እንደተደረገባቸው ተመላክቷል፡፡

በግምገማው መሰረት በአፈፃፀም ሂደቱ የነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች መለየታቸው ነው የተገለጸው፡፡

በዚህም የማንነትና የይገባኛል ጥያቄ ያለባቸውን አካባቢዎች ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በአፋጣኝና በዘላቂነት ሊፈታ እንደሚገባም ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ከዚህ አኳያ ተፈናቃዮችን በአጭር ጊዜ ወደቀያቸው የመመለስ ጉዳይ ቅድሚያ ተሰጥቶት በሚፈፀምበት አግባብ ለይ መተማመን ላይ መደረሱም ተጠቁሟል።

በተጨማሪም በብሔራዊ ደረጃ ይህን እንዲያስፈፅም የተቋቋመው ኮሚቴ በቋሚ የጊዜ ሰሌዳ እየተገናኘ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለጉዳዩ እልባት እንዲሰጥ በዛሬው ዕለት በተደረገው ስብሰባ መወሰኑን ከብሔራዊ ኮሚቴው የደረሰን መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.