Fana: At a Speed of Life!

ሁሉም የፋይናንስ ሥርዓቶች ደህንነቸዉ የተጠበቀ በመሆኑ ህብረተሰቡ ያለምንም ስጋት መጠቀም ይችላል-ብሄራዊ ባንክ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)በሁሉም የፋይናንስ ተቋማት የሚገኙ የፋይናንስ ሥርዓቶች ደህንነቸዉ የተጠበቀ በመሆኑ ህብረተሰቡ ያለምንም ስጋት የፋይናንስ አገልግሎቶችን መጠቀም መቀጠል እንደሚችል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አስታወቀ፡፡

ባንኩ አያይዞም አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱ ደህንነት የበለጠ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ እና የተረጋጋ ሆኖ እንዲቀጠል አስፈላጊ እርምጃዎችንና የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያዎችን መውሰዱን እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጅታል የባንክ ሥርዓት በጊዜያዊነት መቋረጥን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መግለጫ አውጥቷል፡፡

ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

 

 

መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጅታል የባንክ ሥርዓት ላይ ባጋጠመ ችግር ምክንያት የባንኩ መደበኛ አገልግሎቶች ለተወሰኑ ሰዓታት መቋረጣቸዉ ይታወቃል፡፡

እንደሚታወቀው ቀልጣፋና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ባንኮች በሥርዓቶቻቸዉ ላይ በየጊዜዉ የደህንነት ፍተሻ እንዲሁም የማሻሻያ ሥራዎችን ያከናዉናሉ፡፡ በሥርዓቶቹ ላይ በሚከናወን ለዉጦችና ፍተሻዎችም የባንኮች አገልግሎት አልፎ አልፎ ሊቋረጥ ይችላል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በትናንትና ዕለት የተከሰተዉ የአገልግሎት መቋረጥ ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

ችግሩ ከተከሰተበት ሰዓት አንስቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የባንኩን እና የደንበኞቹን ደህንነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል። በመሆኑም የባንኩ መደበኛ አገልግሎቶች በአጭር ጊዜ ዉስጥ እንዲጀምሩና ባንኩ ወደተለመደው እንቅስቃሴው እንዲመለስ ማድረግ ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተከሰተዉ የአገልግሎት መቋረጥ ባንኩ በመደበኛነት በሥርዓቶቹ ላይ በሚያደርገዉ ማሻሻያና ፍተሻ ምክንያት የተከሰተ እንጂ የባንኩን፣ የደንበኞቹን እንዲሁም አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ክስተት አለመሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

በችግሩ ምክንያት የተከሰቱ የደንበኞች መጉላላትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳቶችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስፈላጊዉን ምርመራ በማድረግ ወደፊት ለህብረተሰቡ የሚያሳዉቅ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት የሚጠቀሟቸዉን ሥርዓቶች ደህንነታቻዉ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ፣ ቀልጣፋና የደንበኞችን ፍላጎት የሚያሟሉ ስለመሆናቸዉ በየጊዜዉ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ በሁሉም የፋይናንስ ተቋማት የሚገኙ የፋይናንስ ሥርዓቶች ደህንነቸዉ የተጠበቀ በመሆኑ ህብረተሰቡ ያለምንም ስጋት የፋይናንስ አገልግሎቶችን መጠቀም መቀጠል ይችላል፡፡

የፋይናንስ ተቋማትም የሥርዓቶቻቸዉን ደህንነትና ቀልጣፋነት ይበልጥ ለማሳደግ የቴክኖሎጂ ተለዋዋጭ ባህርይ በማየት በቀጣይነት መሥራት እንደሚኖርባቸዉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጥብቅ ለማሳሰብ ይወዳል፡፡ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱ ደህንነት የበለጠ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ እና የተረጋጋ ሆኖ እንዲቀጠል አስፈላጊ እርምጃዎችንና የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያዎችን መዉሰዱን ይቀጥላል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.