Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ የነዳጅ ተጠቃሚ መኪኖችን መጠን የሚገድብ ህግ ይፋ አደረገች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር የነዳጅ ተጠቃሚ መኪኖችን መጠን የሚገድብ ህግ ይፋ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ሕጉ በፈረንጆቹ 2032 ከአሜሪካ መኪኖች 56 በመቶ የሚሆኑት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንዲሆኑ የሚያደርግ ሲሆን አላማውም የኤሌክትሪክ መኪኖችን ቁጥር በማብዛት የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በመሆኑም የመኪና አምራች ኩባንያዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑ የመኪና ምርቶቻቸውን ቁጥር የኤሌክትሪክ እንዲያደርጉ የተወሰነ ሲሆን ይህን የማያደርጉ የመኪና አምራች ኩባንያዎች ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡

የሀገሪቱ አካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ÷ በጆ ባይደን አስተዳደር ይፋ የተደረገው የነዳጅ ተጠቃሚ መኪኖች ገደብ ህግ 7 ቢሊዮን ቶን የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀትን እንደሚያስቀር ገልጿል፡፡

በዚህም ውሳኔው ከዓመት ዓመት የካርበን ልቀት መጠንን በመቀነስ የአየር ብክለትን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ኤጀንሲው ጠቁሟል፡፡

ይህ የባይደን አስተዳደር ውሳኔ አሜሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከአውሮፓ ህብረት እና ከእንግሊዝ በመቀጠል በነዳጅ ተጠቃሚ መኪኖች ላይ እርምጃ የወሰደች ሀገር እንድትሆን አስችሏታል ተብሏል፡፡

በአሜሪካ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች በዝቅተኛ መጠን እንደሚመረቱ የተገለፀ ሲሆን ባለፈው ዓመት ብቻ ከጠቅላላ የመኪና ምርቶች የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች የተመረቱት ስምንት በመቶ ብቻ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.