Fana: At a Speed of Life!

ኮማንድፖስቱ በፅንፈኛው ቡድን ታግተው የነበሩ 271 ዜጎችን አስለቀቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎጃም ኮማንድፖስት አንድ ኮር በፅንፈኛው ቡድን ታግተው የነበሩ 271 ዜጎችን አስለቀቀ።

ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ ዞን ተነስተው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለስራ በአራት አውቶብስ ተጭነው ሲጓዙ የነበሩ 273 ዜጎች በአማራ ክልል በምስራቅ ጎጃም ዞን በደብረ ማርቆስ እና በኤሊያስ ከተማ መካከል ሲደርሱ በጽንፈኛ ሀይሉ እገታ ተፈጽሞባቸው እንደነበር ኮማንድ ፖስቱ አስታውሷል።

ዘራፊው ቡድን ከሦስት ሰዓት በላይ ወደማይታወቅ ቦታ አስገድዶ ከወሰዳቸው በኋላ ሁለቱን በመረሸን ለቀናት ደብቆ ሲያሰቃያቸው ቆይቷል ብሏል።

መረጃው የነበረው ኮሩ ወደ አካባቢው ተሰማርቶ ከበባ በማድረግ ምቹ ሁኔታ ሲጠባበቅ መከበቡን የተረዳው ጽንፈኛው ለቋቸው ሊሸሽ መቻሉን ገልጿል።

በፅንፈኛ ሃይሎች ከታገቱት መሐል አቶ ዳኛቸው ወርቁ፣ አቶ ኪዳነ ሐድጉ እንዲሁም አቶ አንድአርጌ አሰፋ፤ ፅንፈኛው በበረሀ ውስጥ በአስከፊ ሁኔታ አፍኗቸው የሀይል ጥቃት እንደፈጸመባቸው ተናግረዋል።

ድርጊቱን የተቃወሙ ሁለት መንገደኞችም መረሸናቸውን መግለጻቸውን የመከላከያ ሰራዊት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ አመልክቷል።

ጽንፈኛው ለሠላም እና ለሀገር የሚጠቅም ተግባር የሌለው መሆኑን አሳይቷል ያሉት ታጋቾቹ፤ ህግን በመጣስ በሚፈፀሙ ማንኛውም የወንጀል ድርጊቶች ውጤታቸው ጎጂ ከመሆናቸው ውጪ ሊያመጡት የሚችሉት መፍትሄ እንደማይኖር ገልጸዋል።

እንዲሁም ማንኛውንም ሀሳብ አፈሙዝ አንስቶ በመዋጋት ሳይሆን ለሠላም ቅድሚያ በመስጠት በመነጋገር ሊፈታ ይገባል ብለዋል።

ሠራዊቱ እና የአማራ ክልል የፀጥታ ሀይል ካገኛቸው በኋላ ደህንነታቸው መጠበቁን ጠቅሰው፤ የህዝብን ሠላም ለማረጋገጥ ከሚሰራው ሠራዊት ጎን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊቆም እንደሚገባ አመልክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.