በኢትዮጵያ የሞባይል አገልግሎት ደንበኞች ቁጥር 85 ሚሊየን ደርሷል ተባለ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የመንግስትና የግል የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች ደንበኞች ቁጥር 85 ሚሊየን መድረሱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ ስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች በተገኙበት ዲጂታል ኢትዮጵያን ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራትና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።
በመድረኩ በነበረው የፓናል ውይይት ላይ የተሳተፉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በግልና በመንግስት የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች የሞባይል አገልግሎት ደንበኞች ቁጥር 85 ሚሊየን መድረሱን ተናግረዋል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2018 በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 17 ሚሊየን የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 41 ሚሊዮን መድረሱን ተናግረዋል።
በመንግስትና በግል አጋርነት በተሰራ ማስፋፊያ 6 ነጥብ 3 ሜጋዋት (አይቲ ሎድ) የመሸከም አቅም ያለው የዳታ ማዕከል መገንባቱን ጠቅሰው ይህም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳለው ነው ያነሱት፡፡
የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ የዲጂታል ክፍያን ማሳደግ የተገነባውን መሰረተ ልማት እሴት እንዲጨምር ማድረግ የተቻለበትን አሰራርም ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው÷ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ለማሳካት በጤናው ዘርፍ፣ ስማርት ሲቲ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ ግብር፣ በፍትህ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ከማድረግ ጎን ለጎን ለሳይበር ደህንነት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳሬክተር ትዕግስት ሃሚድ ናቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ በመሬት፣ በግንባታ ፈቃድ፣ በወሳኝ ኩነትና ሌሎች ዘርፎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማሳለጥ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ጠቅሰዋል።