ፈረንሳይ ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥገና እያደረገ ያለው ድጋፍ አበረታች መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥገናን ጨምሮ ለተለያየ ልማት የፈረንሳይ መንግስት እያደረገ ያለው የትብብር ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑ ተገለጸ።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በኢትዮጵያ ከፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሪሾ ጋር በልማትና ድጋፍ ዙሪያ በባህርዳር ከተማ ተወያይተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ላይ እንዳሉት÷ የፈረንሳይ መንግስት በክልሉ እየተካሄዱ ያሉ የቱሪዝም፣ የጤናና ሌሎች ልማቶችን በመደገፍ ረገድ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው።
ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥገና፣ ለደሴ ሆስፒታልና ለግብርና ልማት መፋጠን በፈረንሳይ መንግስት የተደረገውን ድጋፍ በአብነት ጠቅሰዋል።
በክልሉ በሰው ሰራሽ በተፈጥሮ ችግር ለተጎዱ ወገኖች በፈረንሳይ መንግስት እየተደረገ ያለው ሰብአዊ የትብብር ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ርዕሰ መስተዳድሩ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሪሾ በበኩላቸው÷ በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ምርጥ ዘር በማቅረብ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ሀገራቸው እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል።
ይህም የክልሉን ኢኮኖሚ ለማጠናከር እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በቅርስ ጥገና፣ በጤናና ሌሎች የልማት መስኮች የሚደረገው ድጋፍ እንደሚጠናከርም ገልጸዋል።