በሰሜን ጎንደር ከ500 በላይ የታጠቁ ሃይሎች የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመለሱ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ500 በላይ የሚሆኑ የታጠቁ ሃይሎች የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው በመግባት ወደ መደበኛ ሥራቸው መመለሳቸውን የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲ/ን ሸጋው ዉቤ ገለጹ፡፡
ዋና አስተዳዳሪው በዞኑ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ ፥ በወቅቱ በተከሰተው ችግር የሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች መድረሳቸውን አንስተዋል።
በክልሉ እና በዞኑ ጽንፈኛ ኃይሉ የሚፈልገውን ያልተገባ ምኞትና ፍላጎት ለማሳካት ህዝቡን ሰላም በመንሳትና አካባቢው ተረጋግቶ ህዝቡ ወደ ልማት እንዳይገባ ማድረጉንም ነው የጠቆሙት፡፡
መደበኛ የመንግስት ተግባራት በታቀደላቸው መሠረት እንዳይከናወኑ ፣ የፌደራል መንግስት ፕሮጀክቶች እንዳይሰሩ፣ የትምህርት ቁሳቁስ እንዳይሟሉ እንዲሁም የቱሪዝም እንቅስቃሴው ተገድቦ እንዲቆይ አድርጓልም ብለዋል ፡፡
በዚህም ዞኑ የኑሮ ውድነት ችግር መባባስን ጨምሮ ከፍተኛ ችግር ተጋርጦበት እንደነበር ዲ/ን ሸጋው ውቤ የተናገሩት፡፡
በአሁኑ ወቅት ግን በዞኑ አንጻራዊ ሠላም መስፈኑንና ይህ ሰላም እንዲመጣ የህብረተሰቡ አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን በመጠቆም ከ500 በላይ የሚሆኑ የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው በመግባት ወደ መደበኛ ሥራቸው እንደተመለሱ ገልጸዋል፡፡
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ፣ ማህበራዊ ተቋማት ተግባራቸውን እየፈጸሙ እና የተቋረጡ የልማት ስራዎችም መጀመራቸውን መናገራቸውን ከዞኑ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለአካባቢው ሠላም ጠንቅ ከመሆን፣ የአካባቢው ልማት እንዲቀጥል ከተፈለገ የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ ለመንግስት እጅ በመስጠት በሰላም ከማህበረሰቡ ጋር መኖር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡