Fana: At a Speed of Life!

በእገታ፣ በዘረፋ እና በተለያዩ ወንጀሎች ተሳትፈዋል የተባሉ 12 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በእገታ፣ በዘረፋ እና በተለያዩ የማጭበረበር ወንጀሎች የተሳተፉና የተለያዩ 16 የወንጀል ዓይነቶችን የፈፀሙ በአንድ ቡድን የተደራጁ 12 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ የፌደራል ፖሊስ ገለጸ፡፡

በፌደራል ፖሊስ የሚመራው የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ውጤት እያስመዘገበ ተጠናክሮ መቀጠሉን ፖሊስ  ገልጿል።

ፖሊስ በመግለጫው ፥ በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ከጥር 29 እስከ አሁን በቀጠለው ኦፕሬሽን በቁጥጥር ሥር በዋሉ ተጠርጣሪዎች ላይ 2 ሺህ 763 የምርመራ መዝገብ ማደራጀቱንም ነው ያስታወቀው፡፡

በእገታ፣ በዘረፋ እና በተለያዩ የማጭበረበር ወንጀሎች የተሳተፉና የተለያዩ 16 የወንጀል ዓይነቶችን የፈፀሙ በአንድ ቡድን የተደራጁ 12 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ገልጿል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ፖሊስ የምርመራ ውጤቱን በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግም ጠቁሟል፡፡

እንዲሁም የወንጀል ተግባር ሲፈፀምባቸው የተያዙ 20 ተሸከርካሪዎችና ሁለት ሞተር ሳይክሎች፣ 58 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከ509 መሰል ጥይቶች ጋር እንደተያዙ ጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም 67 የተለያዩ ሽጉጦች ከ427 መሰል ጥይቶች፣ በርካታ የኤፍ ዋን ቦንብ ስብርባሪ እና ልዩ ልዩ የጦር መሣሪያዎች፣ የተሰረቁ 66 ላፕቶፕ፣ 28 ታብሌት፣ 2 ሺህ 986 የሞባይል ስልኮችም ተይዘዋል ተብሏል፡፡

ለሕገ-ወጥ ተግባር ሲጠቀሙባቸው የነበሩ 103 ሲም ካርዶች፣ የተሰረቁ በርካታ የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎች፣ 23 ቴሌቪዥኖች፣ የኤሌክትሪክ ገመዶች እና ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 5 ሚሊየን ብር እና 3 ሺህ 500 ዶላርን ጨምሮ የ15 ሀገራት ልዩ ልዩ ገንዘቦችም ከተያዙት ውስጥ ይገኙበታል ተብሏል፡፡

በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ የከበሩ ማዕድናት፣ 208 ሚሊየን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው በኮንትሮባንድ ወደ ሀገር የገቡ መድኃኒቶች፣ ለወንጀል መንስኤ የሆኑ ከ2 ሺህ በላይ የሺሻ እቃዎች እና አደንዛዥ ዕፆች በተካሄደ ኦፕሬሽን ተይዘው ታዛቢዎች በተገኙበት እንዲቃጠሉ ተደርጓል ብሏል ፖሊስ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ መሆኑን የገለፀው ፖሊስ ÷ በአዲስ አበባ ከተማ የተደራጁ ወንጀሎችን በተቀናጀ ኦፕሬሽን መቆጣጠር የሚያስችል ስምሪት ተጠናክሮ የቀጠለ እና በቀጣይም በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ሕዝባዊ፣ መንግስታዊ እና ሐይማኖታዊ ሁነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ ዝግጅት አድርጎ የተጠናከረ ጥበቃ ላይ እንደሚገኝ ፖሊስ በመግለጫው አረጋግጧል።

ኅብረተሰቡ ለፖሊስ መረጃ በመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርቧል።

ንብረት የተወሰደባቸውግለሰቦች በአቅራቢያቸው በሚገኝ ፖሊስ መምሪያ ማስረጃ እያቀረቡ ንብረታቸውን እንዲወስዱም ፖሊስ አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.