Fana: At a Speed of Life!

ተገቢ ያልሆነ ዝቅተኛ የቅጣት ውሳኔ የሰጠ ዳኛ ከሥራ ታገደ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአንዲት ሕጻን ክብረ ንጽህና ላይ ወንጀል መፈጸሙ በተረጋጠ ተከሳሽ ላይ የስድስት ወር ቀላል የእስራት ቅጣት የወሰነ የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛን ከሥራ ማገዱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

በመተከል ዞን ወምበራ ወረዳ ደብረዘይት ከተማ ታኅሣስ 2016 ዓ.ም ተክለአብ ገለታ የተባለ የ17 ዓመት ወጣት በሕጻኗ ክብረ ንጽህና ላይ የወንጀል ድርጊት መፈጸሙ በሕክምና ማስረጃ መረጋገጡን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ሰንበታ ቀጄላ ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የወንጀሉ ክስ የቀረበለት የመተከል ዞን የወምበራ ወረዳ ፍርድ ቤት÷ ሰሞኑን በዋለው ችሎት በተከሳሹ ላይ የስድስት ወር ቀላል እስራት ቅጣት ወስኗ ብለዋል።

የዳኞች አሥተዳደር ኮሚቴ በበኩሉ የወንጀል ድርጊቱ እስከ 10 ዓመት ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ እንደሚችል ጉዳዩን አጣርቶ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሪፖርት አቅርቧል ነው ያሉት፡፡

ውሳኔው ሕዝቡ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ አመኔታ እንዲያጣ የሚያደርግ ሆኖ በመገኘቱ÷ ውሳኔውን ያሳለፈው ዳኛ ከመጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከሥራ እና ደመወዝ መታገዱን አስታውቀዋል፡፡

የወረዳው ዐቃቤ ሕግ በወንጀል ክሱ መዝገብ በተሰጠው የቅጣት ውሳኔ ላይ ለመተከል ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ መጠየቁንም ጠቁመዋል፡፡

ወንጀል ፈጸሚው 17 ዓመት ቢሆነውም የፍርድ ሂደቱ በመደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ የሚታይ ሲሆን÷ ቅጣቱ የሚፈጸመው ደግሞ በወጣት ጥፋተኞች ማረሚያ ማዕከል መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.