Fana: At a Speed of Life!

በአፋር ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ የለማው የስንዴ ምርጥ ዘር ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ አማካኝነት በዱብቲ ወረዳ በ170 ሄክታር መሬት ለመጀመሪያ ጊዜ የለማው የስንዴ ምርጥ ዘር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በተገኙበት ተሰብስቧል።

ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ኢንተርፕራይዙ ከተመሰረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ እዚህ ደረጃ ላይ በመድረሱ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ክልሉ በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል ያሉ አቶ አወል አርባ፤ የእርሻ ትራክተርን ጨምሮ ለኢንተርፕራይዙ የሚያስፈልጉትን የግብርና መሳሪያዎች ድጋፍ በማድረግ ተግባሩን እናጠናክራለንም ብለዋል።

በግብርና ተሠማርቶ ለውጥ አመጣለሁ የሚል አካልን ማገዝና መደገፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ የክልሉ መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የክልሉ እንስሳት፣ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሃም ሙሳ ኢንተርፕራይዙ በአነስተኛ ደረጃ የጀመረውን የምርጥ ዘር ብዜት ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚጥር ተናግረዋል።

ኢንተርፕራይዙ የክልሉ ከፊል አርብቶ አደር ሕዝብ የግብርና ምርታማነት ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል በመሆኑ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል።

የአፋር ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱ ሐሰን በበኩላቸው ኢንተርፕራይዙ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ተቋማት የፋይናንስና ሌሎች ድጋፎችን እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.