የተመዘገቡ ስኬቶች የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ ናቸው – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶች የኢትዮጵያን ብልጽግና አይቀሬነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን በብልጽግና ፓርቲ የፌዴራል ተቋማት አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
የፌዴራል ተቋማት የብልጽግና ፓርቲ አባላት ማጠቃለያ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ብልጽግና የዘመናት የፖለቲካ ስብራትን በዕውቀት እና በእውነት እየጠገነ እንደሚገኝም ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡
ፓርቲው ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ ጠንካራ ተቋማት እንዲገነቡ በመሥራት ላይ መሆኑን ጠቁመው÷ ሐሳብን ወደ ተግባር በመለወጥ ረገድም አመርቂ ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ለሌሎች ሀገራት የዕድገት መሰረት የሆኑ ቴክኖሎጂዎች እና ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር በሀገር በቀል እሳቤ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተጋ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያዊ መልክ ያለው፣ ኅብረ-ብሔራዊ መሆኑን በመግለጽ÷ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ፓርቲው በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን በመጥቀስ ለአብነትም በሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በርካቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት ማከናወን መቻሉን አብራርተዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ የዜጎችን ክብር፣ የሀገርን ሉዓላዊነት እና የኢትዮጵያን ልዕልና ለድርድር እንደማያቀርብም አረጋግጠዋል።
የአይቻልም መንፈስን በተጨባጭ ሥራዎች መስበሩን ጠቁመው በግብርና፣ በአረንጓዴ ዐሻራ እና በሌሎች ዘርፎችም አርዓያ የሚሆኑ ተግባራት ማከናወኑን ነው የገለጹት፡፡
ፓርቲው በአመለካከት እና በተግባር ደረጃ የገጠሙትን ተግዳሮቶች በድል እያለፈ መሆኑን ገልጸው÷ ያስመዘገባቸው ስኬቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው በትጋት ይሠራል ነው ያሉት፡፡
የፓርቲው አባላት በተሰማሩበት ቦታ ሁሉ ጠንካራ ፓርቲ እውን እንዲሆን መስራት እንዳለባቸው አሳስበው÷ ባለፋት ጊዜያት የተመዘገቡ ስኬቶች የብልጽግናን አይቀሬነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
የሕዝቡን የመልማት እና የማደግ ፍላጎት ለማረጋገጥና የኢትዮጵያን ብልጽግና ዕውን ለማድረግ በቀጣይም በመደመር እሳቤ በርካታ ሥራዎች እንደሚሠሩ አመላክተዋል፡፡