Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብ ሀገራዊ ሀብት መፍጠር የሚያስችል ወሳኝ ተግባር ነው – አምባሳደር ስለሺ በቀለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዳሴ ግድብ የሚያስፈልገውን የኢነርጂ መሰረት በመገንባት ዕድገት፣ ብልጽግና እንዲሁም ሀገራዊ ሀብት መፍጠር የሚያስችለን ወሳኝ ተግባር ነው ሲሉ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር) ተናገሩ።

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት 13ኛ ዓመት ‘በህብረት ችለናል’ በሚል መሪ ሀሳብ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የተለያዩ አደረጃጀት አመራሮች እንዲሁም ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ለህዳሴ ግድቡ አስተዋጽኦ ያደረጉ የዳያስፖራ አባላት ተሳትፈዋል።

በበዓሉ ላይ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ የህዳሴ ግድብ ሁሉም ዜጋ ሀብቱን፣ ዕውቀቱንና ጊዜውን በማስተባበር እየገነባው ያለ ልዩ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡

ግንባታው የሀገራችንን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ብሎም ለህዝቦቿ የሚያስፈልገውን የኢነርጂ መሰረት በመገንባት ዕድገት፣ ብልጽግና እንዲሁም ሀገራዊ ሀብት መፍጠር የሚያስችል ወሳኝ ተግባር ነው ሲሉም ገልፀዋል።

ፕሮጀክቱ ከጅምሩ አንስቶ እስካሁን ድረስ ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ጊዜያቸውን ሳይሰስቱ የበኩላቸውን ድርሻ ለተወጡ የዳያስፖራ አባላት ምስጋና አቅርበዋል።

አምባሳደሩ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ይኸው ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ መግለፃቸውን የዘገበው ኢዜአ፤ በዕለቱ ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም መካሄዱን ጠቁሟል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.