መሰናክሎችን ወደ ዕድልነት ቀይረን አያሌ ድሎችን ተቀዳጅተናል – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24፣2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዕልፍ ፈተናዎች ውስጥ አልፈን ቃላችንን ተግብረን ለውድቀት የተዘረጉ መሰናክሎችን ወደ ዕድልነት ቀይረንን አያሌ ድሎችን ተቀዳጅተናል ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ እንኳን ለዴሞክራሲና ብልጽግና አዲስ ምዕራፍ ስድስተኛ ዓመት አደረሰን ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፤ የዘመናት የፖለቲካ ስብራታችን በአዲስ ፖለቲካዊ ዕሳቤ ሊጠገን፣ ደካማ የኢኮኖሚ ዓቅማችን በብዝኃ አማራጮች ሊመነደግ፣ የታመመው ማሕበራዊ መስተጋብራችን በምክክርና በላቀ ሞራል ሊታከም፤ የውጭ ግንኙነታችን ነባር ወረቶቹን ይዞ በአዲስ ዕይታ ብሔራዊ ጥቅማችንን ሊያስጠብቅ በመሪያችን አማካኝነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የዛሬ ስድስት ዓመት ቃል ገብተናል ብለዋል።
ይህንንም ቃላችንን በዕልፍ ፈተናዎች ውስጥ አልፈን ተግብረን ለማሳየት ችለናል በማለት ገልጸው፤ ለውድቀት የተዘረጉ መሰናክሎችን ወደ መስፈንጠሪያ ዕድልነት ቀይረናቸው አያሌ ድሎችን ተቀዳጅተናል ሲሉ ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን የመበልፀግ ራዕይ በፍፁም አገልጋይነት መንፈስ ከዳር ለማድረስ ያለንን ቆራጥነት ዛሬም እናድሳለን ብለዋል።