Fana: At a Speed of Life!

የህግ ማስከበር ስራ ውጤት እያመጣ በመሆኑ ሰላም እና መረጋጋት ለመምጣት የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እየተከናወነ ያለው የህግ ማስከበር ስራ ውጤት እያመጣ በመሆኑ ሰላም እና መረጋጋት ለመምጣት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ እንዲሁም የለውጥና የብልጽግና ዓመታት ጉዞን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም፤ መንግስት በሰላማዊ የመፍትሄ አማራጭ ችግሮችን በድርድርና በውይይት ለመፍታት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይህ አማራጭ ተቀባይነት ሲያጣ የሀገሪቱ ህግ በሚፈቅድለት አኳኋን ህግ የማስከበር ስራ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።

ይህም በመሆኑ በአብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር መቻሉን ገልጸው፤ ይህንን ይበልጽ ማጽናት፣ መጠበቅና ዘላቂነቱን ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል የተጀመረው የህግ ማስከበር ስራ ውጤታማነቱን ጠብቆ መቀጠሉን ገልጸው፤ ክልሉም ከሞላ ጎደል ወደ ተሟላ ሰላም እና መረጋጋት ለመምጣት የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሮለታል ብለዋል፡፡

12 ሺህ የሚሆኑ የታጠቁ ሃይሎች መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ተሃድሶ በመውሰድ ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ከ10 ሺህ ያላነሱ የቀድሞ የክልሉ ልዩ ሃይል አባላትም በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት በተሃድሶ ስልጠናዎች አልፈው ክልሉን ከጥፋት ሃይሎች ለመታደግ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

በሌላ በኩል የሽብር ቡድኑ ሸኔ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው፤ በመጋቢት ወር ቡድኑ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ላይ የመከላከያ ሰራዊት ባደረገው አሰሳ እና ዘመቻ መጠነ ሰፊ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት መደምሰሳሰቸውን እና ለበርካታ አመታት ቡድኑ በብቸኝነት የተጠቆጣጠሯቸው ዋሻዎች፣ ጫካዎች እንደ መደራጃ፣ የሎጂስቲክስ ማከማቻ እና ማሰልጠኛ የሚጠቀሙበትን መቆጣጠሩን ገልፀዋል፡፡

በአጠቃላይ በተሰራው የህግ ማስከበር ስራ በተገኘው ውጤት ሰላም እና መረጋጋት ለመምጣት የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.