Fana: At a Speed of Life!

ገጣሚ ለምን ሲሳይ ከመቅደላ የተዘረፉ ቅርሶች እንዲመለሱ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እንግሊዝ ውስጥ ታዋቂ የሆነው ገጣሚ ለምን ሲሳይ ከመቅደላ የተዘረፉ ቅርሶች እንዲመለሱ ጠየቀ።

ከመቅደላ ተወስደው በእንግሊዝ የሚገኙ ቅርሶች እንዲመለሱ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸውና በእንግሊዝ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊውያን አርቲስቶችም ቅርሶቹ እንዲመለሱ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክቷል።

በጣሊያን ቬነስ ከተማ በተካሄደው በዓለም አቀፉ የቢናሌ የባህል ኤግዚቢሽን ተገኝቶ ግጥሞቹን ያቀረበው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ገጣሚና ደራሲ ለምን ሲሳይ፤ ከዘጋርዲያን ጋር ባደረገው ቆይታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ አርቲስቶች በእንግሊዝ እንደሚኖሩ ተናግሯል።

እሱን ጨምሮ እንደ ዘዊኬንድ እና ሩት ነጋን የመሳሰሉ አርቲስቶች በእንግሊዝ እና በአየርላንድ እንደሚኖሩ በአብነት አንስቷል።

ከተጠቀሱት በተጨማሪ ሌሎች የኪነ ጥበብ ቤተሰብ የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በእንግሊዝ እንደሚኖሩ ገልጾ፤ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ያላቸውን ተጽዕኖ ፈጣሪነት በመጠቀም በእንግሊዝ ጦር ከመቅደላ ተዘርፈው የተወሰዱ ቅርሶችን ማስመለስ እንደሚቻል አስረድቷል፡፡

በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት በፈረንጆቹ 1868 የእንግሊዝ ጦር በርካታ ንዋየ ቅድሳት መዝረፉን ጠቅሶ፤ ቅርሶቹን ለማስመለስ የተደረገው ጥረት አነስተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ጣሊያን ቬነስ ከተማ በተካሄደው ዓለም አቀፉ የባህል ኤግዚቢሽን ላይ ከእርሱ ግጥም በተጨማሪ የትውለደ ኢትዮጵያዊው ሰዓሊ ተስፋየ ኡርጌሳ ስዕሎች ለዕይታ መቅረባቸውን ገልጿል፡፡

ይህም የኢትዮጵያን ባህል ከማስተዋወቅ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የገለፀው አርቲስቱ÷ ዳያስፖራው ባለፉት 20 ዓመታት የኢትዮጵያን ባህል ለማስተዋወቅ የጀመረውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ እና በጣሊያን መካከል ያውን ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን አመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ በታሪኳ ቅኝ ተገዝታ እንደማታውቅ የገለፀው ለምን ሲሳይ÷ ቅርሶቹ ሲመለሱ የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት ታሪክ፣ ሀይማኖት፣ ባህል እና ወግ የሚዘክሩ እንጂ ሌላ የበደል አስታዋሾች አለመሆናቸውንም አስገንዝቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.