ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የሚያግዛትን ድርድር በግንቦት ወር ታካሂዳለች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የሚያግዛትን 5ኛ ዙር ድርድር በግንቦት ወር እንደምታካሂድ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረ መስቀል ጫላ ገለፁ።
ኢትዮጵያ ከ20 ዓመታት በፊት የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እንቅስቃሴ የጀመረች ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ድርድሩ ተቋርጦ መቆየቱን አቶ ገብረ መስቀል ጫላ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የጀመረችውን ጥረት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከቆመበት ለማስቀጠል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በሐምሌ 2015 ዓ.ም ወደ ጄኔቫ አቅንተው ከድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
በውይይቱም ኢትዮጵያ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የድርድር ሂደቱ እንዲጠናቀቅና የድርጅቱ አባል እንድትሆን ከሥምምነት መደረሱንም ጠቁመዋል።
በዚህም ከኢትዮጵያ ጋር ድርድር ለማድረግ ፍላጎት ካላቸው አባል ሀገራት 180 የሚጠጉ ጥያቄዎችና 9 ሰነዶች መቅረባቸውን ተናግረዋል።
በቅርብ ጊዜ ውስጥ ድርጅቱ በሚያመቻቸው መድረክ ድርድሩ እንደሚጀመር ሚኒስትሩ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን የሀገሪቱን ጥቅም በሚያስጠብቅ እንዲሁም የኢኮኖሚ ልማትና የንግድ ተወዳዳሪነት በሚያረጋግጥ አግባብ ለመደራደር ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።