ባለፉት ዓመታት የገጠሙንን ፈተናዎች በማለፍ በርካታ ስኬቶችን አስመዝግበናል- አቶ ፍቃዱ ተሰማ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር የገጠሙንን ፈተናዎች በማለፍ በርካታ ስኬቶችን አስመዝግበናል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ተናገሩ፡፡
ዛሬ በቄለም ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ ከተማ የተገነባው ባለ ሶስት ወለል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ህንፃ ተመርቋል፡፡
በዚህ ወቅት አቶ ፍቃዱ ÷ዞኑ የነበረበትን የሰላም እጦት ችግር በመቋቋም ይህን የመሰለ ህንፃ ማስገንባት የጠላቶችን እሳቤ ያከሸፈና ፓርቲው የጀመረውን የብልጽግና ጉዞ እውን ማድረጉን እንደሚያስቀጥል ማሳያ ነው ብለዋል።
እንደ ዞን ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ባለፉት ዓመታት ብዙ ፈተናዎች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ፍቃዱ፤ እነዚህ ፈተናዎችን በማለፍ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ የተቻለበት እንደሆነ ተናግረዋል።
ከእነዚህ ስኬቶች ውስጥም የህዳሴውን ግድብ ወደ ፍፃሜው ማድረስ፣ብሎም ኢትዮጵያ ከስንዴ ልመና ወጥታ ስንዴን ወደ ወጭ የምትልክ ሀገር ማድረግ የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።
በቄለም ወለጋ ያለውን የፀጥታ ችግር በመፍታትም አካባቢውን የልማት ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የዚህ ማሳያ አንዱ በቅርቡ ስራ የጀመረው የደምቢዶሎ አውሮፕላን ማረፊያ መሆኑን ተናግረው ሌሎች በፀጥታ ችግር ምክንያት የተቋረጡ በርካታ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ህዝቡም የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ እገዛውን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በዛሬው እለት በደምቢ ዶሎ ከተማ ለተመረቀው የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ህንፃ ግንባታ ከ47 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን 23 ሚሊየን ብር ደግሞ ለስራ ለሚያስፈልጉ እቃዎች ግዢ መዋሉ ተመላክቷል፡፡
በታሪኩ ለገሰ