የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ዋና ጽሕፈት ቤት በአማራ ክልል ለተጎዱ ሴቶች ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ዋና ጽሕፈት ቤት በአማራ ክልል በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ለተጎዱ ሴቶች የሚውል የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
የሊጉ ኃላፊ እሌኒ ዓባይ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የሴቶች ሊግ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራ ነው።
በሰሜኑ ጦርነት የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ “አንድ ቤተሰብ ለአንድ ቤተሰብ” በሚል ሃሳብ ገቢ በማሰባሰብ ከ7 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።
በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመቀልበስ እና ሰላምን ለማረጋገጥ መሠራቱን ገልፀው፥ “የኢትዮጵያን ሰላም አስጠብቃለሁ፣ ለልጆቼ ምንዳን አወርሳለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ ውይይቶች መደረጋቸውንም ነው ያነሱት።
የሊጉ ም/ፕሬዚዳንት እና የጽ/ቤት ኃላፊ መስከረም አበበ በበኩላቸዉ፥ ሊጉ ክልሎችን በማስተባበር እና ከኅብረተሰቡ ሃብት በማሰባሰብ ለተጎዱ ቤተሰቦች ሲደርስ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
“ሁለት መቶ ለእናቴ አንድ እቃ ለአንድ ተፈናቃይ” በሚል መሪ ሃሳብ በተደረገ ሀገራዊ ንቅናቄ የተሰበሰበውን ሀብት ለሚመለከታቸው አካላት ማድረሳቸውንም ገልፀዋል።
ከተሰበሰበው ገንዘብ መካከል 6 ሚሊየን ብር የሚሆነውን ለአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሴቶች ሊግ ማስረከባቸውን ነው የተናገሩት።
የተደረገውን ድጋፍ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች ማድረስ እንደሚገባ ገልጸው፥ ሊጉ ድጋፉን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በም/ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)፥ ድጋፉ በችግር ዉስጥ የሚገኙ ሴቶችን ለማቋቋም አፈጻጸም፣ መመሪያና የአሰራርና የተጠያቂነት ስልት እንዘረጋለን ብለዋል፡፡
በዚህም የተሠጠውን ድጋፍ ለተገቢው ዓላማ ለማዋልና ሴቶችን ለማቋቋም እንደሚሠራ መናገራቸውን ከብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።