ቻይና የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የሚያከናውናቸውን ተግባራት እንደምትደግፍ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና መንግስት የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ገለጸ፡፡
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ኢኮኖሚክ ካውንስለር ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ኮሚሽነር ተመስገን የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የተሰጡትን ተልዕኮዎች ለመወጣት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን አብራርተዋል።
በኮሚሽኑ የታቀዱ ተግባራት ከፍተኛ ሃብት፣ ቅንጅት እና ትብብርን የሚጠይቁ መሆኑን ጠቅሰው÷ ለፕሮግራሙ ስኬት የቻይና መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
የቻይና ኤምባሲ ኢኮኖሚክ ካውንስለር ያንግ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የቻይና መንግስት ኢትዮጵያ የምታከናውናቸውን ዘርፈ-ብዙ የሰላምና የልማት ሥራዎች በመደገፍ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
ኮሚሽኑ በቀጣይ የሚተገብረውን የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ፕሮግራም በታቀደው ጊዜ እንዲሳካ ቻይና የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ አንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።