Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት የህግ ማእቀፍ ተዘጋጅቶለት ይሰራበታል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍትህ ሰርዓቱን ለማገዝ እና ለማጠናከር እንዲሁም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት የህግ ማእቀፍ ተዘጋጅቶለት ይሰራበታል ሲሉ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ተናገሩ፡፡

በደሴ ከተማ በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ የሚገኙ አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ እና ፍትህ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ውይይት እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የተገኙት አፈ-ጉባኤዋ ለገጠመን የሰላም መደፍረስ፣ ፍትህ ለማስፈን በየአካባቢው ማህበረሰቡ የሚገለገልባቸው ባህላዊ እርቅ የሚደረግባቸው የሽምግልና ስርዓቶች ለሁለንተናዊ ሰላም ወሳኝ ድርሻ አላቸው ብለዋል።

በመሆኑም ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውሉ የክልሉ መንግስት የበኩሉን ሚና ይወጣል ሲሉ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዚዳንት አቡየ ካሳው በበኩላቸው በፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ ከማህበረሰቡ ጋር ምክክር ማድረግ በፍትህ እና ዳኝነት ስርዓቱ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ወሳኝ እንደሆነ አንስተዋል።

በተለይም ባህላዊ የዳኝነት ስርዓቶችን በህግ ማዕቀፍ ስር የፍትህ ስርዓቱን እንዲያግዙ ማድረግ ማህበረሰቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።

በእሸቱ ወ/ሚካኤል

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.