Fana: At a Speed of Life!

ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምናደርገው ድጋፍ በሀገር ግንባታ ሥራችን ላይ አሻራ የምንጥልበት ነው – አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የምናደርጋቸው ድጋፎች በሀገር ግንባታ ሥራችን ላይ አሻራ የምንጥልበት በመሆኑ አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ አለብን ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡

አፈ ጉባዔው የምክክር ኮሚሽኑን የአፈፃፀም ሪፖርት ባዳመጡበት ወቅት÷ ኮሚሽኑ ተልዕኮውን ለማሳካት የሚያገጥሙ ችግሮችን በመቋቋም የህዝቦችን ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅ ያከናወናቸውን ሥራዎች አድንቀዋል፡፡

በሀገር ደረጃ ያሉ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ከችግሩ መቅድም ያስፈልጋል ያሉት አፈ ጉባዔው÷ ለሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ተገዢ በመሆን ከመንግስት መዋቅርና ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመመካከር መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ሌሎች ድጋፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ተቋማት ጋር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በጋራ በመስራት ለህዝብ የተገባውን ቃል መፈጸም ይኖርብናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አረአያ (ፕ/ር) በበኩላቸው÷ በክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች በርካታ የቅድመ ዝግጅት እና የተሳታፊ ልየታ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

በክልል ደረጃ የሚደረጉ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ምክክር ሂደቶችን አስመልክቶ የአሰራር ስርአት በመዘረጋት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን አስረድተዋል።

በቀጣይም ኮሚሽኑ የተሳታፊዎች ልየታ ባልተከናወነባቸው ክልሎች ልየታ በማድረግ አጀንዳዎችን በህዝባዊ ውይይቶች በማሰባሰብ ምክክሮች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ሂደት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያግዙ የባህል መሪዎችን የመለየትና ተቀራርቦ የመወያየት ስራዎችን እንሰራለን ማለታቸውን የም/ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

በግጭቶች ምክንያት በክልሎች የተሳታፊዎች ልየታ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ተግዳሮት መግጠሙን አስገንዝበዋል።

በምክክር ሒደቱ ውጤታማ እና በሀገሪቱ የተሻለ የሰላምና የፖለቲካ መደላድል እንዲፈጠር ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረከት ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.