Fana: At a Speed of Life!

በአቡዳቢና ዱባይ ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎች እየተፈቱ እንደሆነ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአቡዳቢና ዱባይ አካባቢ እየተሰጠ ባለው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎቶች ከዚህ ቀደም የሚነሱ ቅሬታዎች እየተፈቱ መሆኑን የኮሚኒቲ አባላት፣ ተወካዮችና አመራሮች ተናግረዋል።

በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት የተመራ ልዑክ በአቡዳቢና ዱባይ ሚሲዮኖች የሚሰጡ የዜግነት አገልግሎቶችን ያሉበትን ሁኔታ ተመልክቶ ከሚሲዮን መሪዎችና ኮሙኒቲ ተወካዮች ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱ በሚሲዮኖቹ ከፓስፖርት እድሳትና ተያያዥ አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ዜጎች ላቀረቡት ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ የሚደነቅ ቢሆንም፤ ከጉዞ ሰነድና ቪዛ ጋር ተያይዞ ያሉ የአግልገሎት አሰጣጥ ችግሮች እንዲፈቱ ተጠይቋል፡፡

በተጨማሪም የመረጃ ልውውጥ ክፍተት፣ ሐሰተኛ ማስረጃ፣ የጉዞ ሰነድ (ሊሴ ፓሴ)፣ የበይነ-መረብ አጭበርባሪዎች መበራከት እንዲሁም ከዜግነት አገልግሎት ጋር ያሉ ክፍተቶች መኖራቸው ተጠቁሟል፡፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት÷ ተቋሙ 11 የሪፎርም አጀንዳዎችን ቀርጾ ወደ ስራ በመግባቱ ከዜጎች አገልግሎት ጋር በተያያዘ እየታዩ ያሉ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች መታየታቸውን ተናግረዋል።

የሪፎርሙ ስራ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ በዘርፉ የተስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

ከሰነድ አልባና ከዜግነት አገልግሎት ጋር ያሉ ስራዎች ከሀገር ደህንነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ በመሆኑ በጥንቃቄና በህግ አግባብ ብቻ መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ልዑኩ ባደረገው ጉብኝት የዱባይ ሚሲዮን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ረገድ የሚከተለው አሰራር እንደተሞክሮ ሊወሰድ የሚገባ መሆኑን እንደተመለከተ ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.