Fana: At a Speed of Life!

የትንሳኤ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ትህትናን፣ ፍቅርንና ይቅርባይነትን በተግባር ያስተማረበት ነው – አቶ አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው÷የትንሣኤ በዓል በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ የሠውን ልጅ ለማዳን መከራ ተቀብሎ በመስቀል ተሰቅሎ፣ ሞቶ መነሣቱን በመዘከር የሚያከብሩት በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

ሕዝበ-ክርስቲያኑ ይህንን በማሰብም ላለፉት ሁለት ወራት በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ማሳለፋቸውን ጠቅሰው÷ ይህም ለሀገር ሠላምና አንድነት ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ፍጹም ትህትናን፣ ፍቅርንና ይቅርባይነት በተግባር ያስተማረበት መሆኑን አውስተው÷ የእምነቱ ተከታዮች ይህንኑ በማሰብም በታላቅ ድምቀት እንደሚያከብሩት ተናግረዋል።

የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ ኃይማኖታዊ አስተምህሮውን በመከተል በሀገራችን ያለው የመከባበር፣ የአብሮነትና የመረዳዳት መልካም እሴት የበለጠ እንዲጎለብት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ሀገራችን የጀመረችው የለውጥ ጉዞ የታለመለትን ግብ እንዲመታ እና የሕዝቦች አብሮነት እንዲጎለብት የእያንዳንዳችን ተሣትፎና ጥረት እጅጉን አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም አሳስበዋል።

መላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሳኤ በዓልን ሲያከብሩ የተቸገሩትን በመደገፍ፣ የሌላቸውን በመርዳት፣ አብሮ በመብላት እና በፍጹም መተሳሰብ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል።

ሀገራዊ አንድነታችንን የበለጠ በማጠናከር ለጀመርነው የብልጽግናና የልማት ጉዞ ስኬት ትልቅ መሠረት የሆነውን ዘላቂ ሠላምን ለመገንባት በጋራ በጋራ መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሳኤ በዓል የሠላም፣ የፍቀር፣ የደስታ፣ የአብሮነትና የመተሳሰብ እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.