Fana: At a Speed of Life!

የ”ኩል ፖርት አዲስ” ፕሮጀክት ግንባታ ዘንድሮ ይጀመራል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአትክልትና ፍራፍሬ ማቆያና መጓጓዣ የሚውለው የ”ኩል ፖርት አዲስ” ፕሮጀክት ግንባታ ዘንድሮ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ባህርና ሎጂስቲክስ አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ባህርና ሎጂስቲክስ የወደብና ተርሚናል ም/ዋና ስራ አስፈጻሚ ምህረተአብ ተክሉ እንደገለፁት፥ የአትክልትና ፍራፍሬ የምርቶችን ጥራት ጠብቆ ወደ ውጪ በመላክ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ የማዝቀዣ ኮንቴነሮችን መገንባት ወሳኝ ነው ፡፡

ከዚህ አኳያ በሞጆ ደረቅ ወደብ የአትክልትና ፍራፍሬ ማቆያና መጓጓዣ የሚውል “ኩል ፖርት አዲስ” ፕሮጀክት መሰረት ድንጋይ ከስድስት ዓመት በፊት መቀመጡን አስታውሰዋል፡፡

ይሁንና ግንባታውን ለመጀመር የሚውል ፋይናንስ በሚፈለገው ጊዜ አለማግኘትና በዘርፉ በቂ ልምድ ለማግኘት የሚያስችሉ ጥናቶች መጓተት ፕሮጀክቱ በተባለለት ጊዜ እንዳይጀመር ማድረጉን አብራርተዋል።

በዚህም ለፕሮጀክቱ ግንባታ የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት ከኔዘርላንድስ መንግስት ጋር ውይይትና ድርድር ሲካሄድ መቆቱን አንስተው ይህን ተከትሎም ከወራት በፊት የ25 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ስምምነት መፈረሙን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ በ50 ሚሊየን ዶላር የሚፈጅ ሲሆን ፥ ቀሪው 25 ሚሊየን ዶላር በኢትዮጵያ መንግስት እንደሚሸፈንም መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

በመሆኑም የፕሮጀክቱ ግንባታ በዘንድሮው ዓመት እንደሚጀመርምና በሁለት ዓመት ወስጥ እንደሚጠናቀቅ አረጋግጠዋል።

በሌላ በኩል በሞጆ ደረቅ ወደብ የነዳጅ አቅርቦቱን አስተማማኝ በማድረግ የካርጎ አገልግሎት ማሳለጥ የሚያስችለውና ከ47 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የነዳጅ ማከማቻ ዲፖ ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣዩ ወር ወደ ስራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.