Fana: At a Speed of Life!

ኅብረተሰቡ የፕላስቲክ ቆሻሻን ለይቶ ለማኅበራት በመስጠት ብክለትን ለመከላከል የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኅብረተሰቡ የፕላስቲክ ቆሻሻን ለይቶ ለተደራጁ ማኅበራት በመስጠት የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የተጀመረውን ዘመቻ እንዲያግዝ የሲዳማ ክልል ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ጥሪ አቀረበ፡፡

“ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ሐሳብ ክልል አቀፍ የንቅናቄ መድረክ በይፋ መጀመሩን እና በንቅናቄውም ለስድስት ወራት የሚከናወኑ የዘመቻ ሥራዎች መኖራቸውን በባለስልጣኑ የአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር ዮሴፍ ቲቦ ተናግረዋል፡፡

የብክለት መነሻ ተብለው የተለዩ የፕላስቲክ፣ የአየር፣ የውሃ፣ የአፈርና የድምጽ ብክለቶች እንዳሉ ጠቁመው÷ ብክለት በአካባቢ ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ከግምት ያስገባ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደትግበራ መገባቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም የፕላስቲክ ብክለት በአካባቢ ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመከላከል ከተደራጁ ማኅበራት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ነው ለኢዜአ የገለጹት፡፡

ማኅበራቱ በተለያዩ ከተሞች የፕላስቲክ ውጤቶችን ሰብስበው መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል በሚቻልበት ሥራ ላይ መሰማራታቸውን እና የንቅናቄው አካል እንዲሆኑም የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሰራቱን አስታውቀዋል፡፡

ፕላስቲክ ከ500 እስከ 1 ሺህ ዓመት አፈር ውስጥ የመቆየት አቅም እንዳለው በጥናት መረጋገጡን አመላክተው÷ በአካባቢ ብክለት ላይ ያለውን ተጽዕኖ ለመከላከል የኅብተረተሰቡ ድርሻ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

ኅብረተሰቡም የፕላስቲክ ቆሻሻን ለይቶ ለተደራጁ ማኅበራት በመስጠት የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የተጀመረውን ዘመቻ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

የፕላስቲክ ውጤቶችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የተደራጁ ማኅበራት በበኩላቸው÷ የአየር ብክለትን ለመከላከል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ንቅናቄ ውጤታማ ለማድረግ በትጋት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.