በባህር በር ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “የባህር መውጫና ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ በባህር በር ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ ምሁራን፣ አባገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በፓናል ውይይቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት በዛብህ ወንድሙ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር÷ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር በተጨማሪ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በምርምር የተደገፉ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይ የሀገር ጥቅምን ለማስጠበቅ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ የሚያተኩሩ ስራዎች ዋነኞቹ እንደሆኑ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በታሪክ ክስተት ከባህር በር ተጠቃሚነቷ እንድትገፋ መደረጓን አስታውሰው፤ ይህ ክስተት ሀገሪቱን በድህነት እንድትቆይና በዓለም መድረክ ተፎካካሪ እንዳትሆን አድርጓታል ብለዋል።
የባህር በር ተጠቃሚነትን የዓለም አቀፉን ህግ በጠበቀ መንገድ ለማግኘት መጠየቅ ፍትሐዊ ጥያቄ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
እነዚህን ፍትሐዊ ጥያቄዎች ለዓለም ለማስረዳት በጥናትና ምርምር ለመደገፍ መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ሀገራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት እየሰራ ነው ብለዋል።
ለፓናል ውይይቱ የመነሻ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ መሀመድ ጀማል (ዶ/ር) የዓለምና ቀጠናዊ አሁናዊ እውነታዎች ኢትዮጵያ የባህር በር መውጫ እንዲኖራት ያስገድዳታል ብለዋል።
ሰላማዊ በሆኑ ሁሉም አማራጮች ዘላቂነት ያለው የባህር በር ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ለዚህ ስኬት ምሁራንና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
በይድነቃቸው ኃ/ማርያም