ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የደቡብ ግንባር ሆስፒታል የግንባታ ሂደትን ጎብኙ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በኦሮሚያ ክልል ቢሻን ጉራቻ ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን የደቡብ ግንባር ሆስፒታል የግንባታ ሂደት ጎብኝተዋል፡፡
የሆስፒታሉን የግንባታ ሂደትና አሁን ያለበትን ደረጃ በተመለከተ በተቋራጩ ገለፃ እንደተደረገ ተገልጿል፡፡
የሆስፒታሉ ግንባታ ከተጀመረ ቅርብ ጊዜ ቢሆንም አሁን ያለበት የግንባታ ደረጃ ጥሩ የሚባልና በተፈለገው ልክ እየሄደ መሆኑን ተናግረው ፥ ሆስፒታሉ በተቀመጠለት ጊዜ ተገንብቶ መጠናቀቅ እንዳለበት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ አሳስበዋል፡፡
በጉብኝቱ ከጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በተጨማሪ የመከላከያ መሀንዲስ ዋና መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼን ጨምሮ የደቡብ ዕዝና የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዦች መገኘታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡