ከየመን ወደ ጂቡቲ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ተገልብጣ የ16 ኢትዮጵያውያን ህይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ትናንት ምሽት ከየመን የባሕር ዳርቻ ልዩ ስሙ ‘አራ’ ከተባለ ቦታ 77 ኢትዮጵያውያን ሕገ-ወጥ ፍልሰተኞችን አሳፍራ ወደ ጂቡቲ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ጎዶሪያ አካባቢ ተገልብጣ የ16 ወገኖች ሕይወት አለፈ፡፡
እንዲሁም አብረው በጀልባዋ ተሳፍረው የነበሩ 28 ኢትዮጵያውያን እስካሁን አለመገኘታቸውን በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል 33 ፍልሰተኞች በሕይወት ተርፈው ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡
ኤምባሲው የተሰማውን ሐዘን ገልጾ÷ ከጂቡቲ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት የሚደረጉ ሕገ-ወጥ ጉዞዎች እጅግ አደገኛ ከመሆናቸውም በላይ በየጊዜው የዜጎችን ሕይወት እያሳጡ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በመሆኑም ዜጎቻችን በሕገ-ወጥ ደላሎች የሐሰት ስብከት በመታለል ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው በዚህ አደገኛ የጉዞ መስመር ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ ሲል አሳስቧል፡፡