Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመስኖ ልማት ከ22 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምርት ዘመኑ በመስኖ ልማት እስካሁን ከ22 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉ ተገለፀ፡፡

ክልሉ ለግብርናው ዘርፍ ምርታማነት ያሉትን የመልማት አቅሞችና ፀጋዎች ታሳቢ ባደረገ መልኩ አቅዶ በመስራት ላይ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን÷ በዚህም በዘርፉ ተጨባጭ ዕምርታዎች እየተመዘገቡ ነው ተብሏል።

በተለይ ክልሉ ያለውን የውሃ ሃብት ከግምት በማስገባት እና ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ በማለም ለመስኖ ልማት ቀዳሚ ትኩረት ተሰጥቶ በተሰራ ስራ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ነው የተባለው።

በምርት ዘመኑ የመስኖ ልማት በአትክልት፣ በሥራሥር፣ በፍራፍሬና በሰብል ልማት ከ125 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ከዕቅድ በላይ መከናወኑም ተመላክቷል፡፡

በዚህም እስካሁን ከ22 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት የተመረተ ሲሆን÷ የምርት ማሰባሰብ ስራው ተጠናክሮ እንደቀጠለ ታውቋል።

በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የግብርና ልማት አጠቃላይ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን ከክልሉ ርእሰ መስተዳድር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.