Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በኢንተርፖል ዓለም አቀፍ ዓመታዊ ኮንፍረንስ ላይ እየተሳተፈች ነው

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በፈረንሳይ ሊዮን ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው 19ኛው የኢንተርፖል ዓለም አቀፍ ዓመታዊ ኮንፍረንስ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡

በኮንፈረንሱ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ብሔራዊ ኢንተርፖልና ዓለም አቀፍ የፖሊስ ትብብር መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ደጀኔ በቀለ፤ ከኮንፈረንሱ ጎን ለጎን ከኢንተርፖል አገልግሎት ማስፋፋት ፕሮጀክት አስተባባሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ÷ በሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ የኢንተርፖል አገልግሎት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ስላለበት ሁኔታና ስለሌሎች ወደ ኢሚግሬሽን፣ ኤርፖርት፣ ጉሙሩክ፣ የድንበር ሴኩሪቲ እና የኢንተርፖል አገልግሎትን ወደ ክልል የፖሊስ ተቋማት በማስፋፋት በድርጅቱ ዳታ ቤዝ የሚገኙ መረጃዎችን በሚጠቀሙበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል፣ የፎረንሲክ እና የሳይበር ወንጀል ምርመራን አጠናክሮ ለማስቀጠል፤ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እያካሄደ ባለው ሪፎረም በተለይ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና በሰው ኃይል አቅም ግንባታ ከኢንተርፖል ጋር በትብብር ለመስራት ምክክር አድርገዋል።

የኢንተርፖል አገልግሎት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ለኢትዮጵያ ፖሊስ የሚያደርገውን የአቅም ግንባታ ስልጠና እና የማቴሪያል ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል መግባቱን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል።

ኮንፍረንሱ የሀገራት የብሔራዊ ኢንተርፖል ቢሮ ኃላፊዎች እና ከፖሊስ ጋር በአጋርነት የሚሰሩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እየተሳተፉ የሚገኙ ሲሆን የየሀገራቱ ኢንተርፖል ቢሮዎች ባለፈው ዓመት ስላከናወኗቸው እና በቀጣይ ስለሚከናወኑ ተግባራት እንዲሁም የሀገራት ተመክሮዎች ላይ ውይይት ተደርጎ ልዩ ልዩ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ ይጠበቃል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.