Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ቻምበር በኢትዮጵያ የግብር አስተዳደርን በማሻሻል ላይ ያተኮረ የፖሊሲ ሰነድ ይፋ አደረገ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የሚገኘው የአውሮፓ ቻምበር በኢትዮጵያ የግብር አስተዳደርን በማሻሻል ላይ ያተኮረ የፖሊሲ ሰነድ ይፋ አደረገ፡፡

የፖሊሲ ሰነዱ በሀገሪቱ የግብር አስተዳደር ሂደት ውስጥ የግሉ ዘርፍ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች እንደሚዳስስ ተገልጿል።

በመድረኩ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀና አርአያ ስላሴ፣ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ፣ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ምክር ቤት የቦርድ ሰብሳቢ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት ነው ፖሊሲ ሰነዱ ይፋ የሆነው።

ከግብር ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ፣ የግብር አሰራር ወጥነትን ለማሻሻል ፣ የሕጎችን የተሳሳተ ትርጓሜ ለማረም እና የኩባንያዎችን የኦዲት አሰራር ለማሻሻል ምክረ ሃሳቦችም ቀርበዋል።

የፖሊሲ ሰነዱ የኢትዮጵያን የግብር አስተዳደር ስርዓት ለማሻሻል ይረዳሉ ያላቸውን ምክረ ሀሳቦች ለመንግስት አቅርቧል።

የፖሊሲ ሰነዱ በአውሮፓ ቻምበር እና በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ በጂአይዜድ በሚተገበረው “በቢዝነስ ኢንቫይሮንመንት እና ኢንቨስትመንት ክላይሜት ኢንክሉዲንግ ኢጋቨርንመንት” ፕሮጀክት ትብብር የተዘጋጀ ነው።

ወጥ የሆኑ የኦዲት አሰራሮችና ኢንዱስትሪ ተኮር የመመሪያ ሰነዶች፣ ለኦዲተሮች ከሚሰጠው አጠቃላይ ሥልጠና ጎን ለጎን ወሳኝ ናቸውም ተብሏል።

በተጨማሪም እነዚህ በመንግስት የሚዘጋጁ መመሪያዎች መሬት ላይ ያለውን የኢንዱስትሪ አሰራር በትክክል የሚያንፀባርቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የግብር ከፋዮችን ማሳተፍ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ግብር በወቅቱና በአግባቡ ለሚከፍሉ የግብር ከፋዮች ፈጣን እና ከሌሎች ቅድሚያ አግኝተው የሚስተናገዱበት አሰራር እንዲዘረጋም ተጠይቋል።

የፖሊሲ ሰነዱ ፍትሃዊ እና የተሻለ ግልጽነት ያለው የግብር አስተዳደር ሂደት እንዲኖር የተጠየቀ ሲሆን ÷ ይህን ማሳካት የሚቻለው የግብር ቅሬታ ለማቅረብ የሚጠየቀውን የገንዘብ መጠን በመቀነስ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

እንዲሁም የግብር ከፋዩ የወጡ መመሪያዎችን ተገንዝቦ እንዲሰራ መደገፍ ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ፣ ለኦዲተሮች ተጨባጭ የግብር አሰባሰብ ግቦችን በማስቀመጥና ተጠያቂ የሚሆኑበትን ግልጽ ዘዴዎችን በመተግበር ነው ተብሏል።

በፍሬህይወት ሰፊው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.