Fana: At a Speed of Life!

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በተመረጡ ከተሞች በኦን ላይን ለመስጠት እየተሠራ መሆኑ ነው – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በተመረጡ ከተሞች በኦን ላይን ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር) ገለጹ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ምክክር መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ፥ የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሙሉ በሙሉ በኦን ላይን ለመስጠት ባይቻልም በሁሉም ክልሎች በተመረጡ ከተሞች ለመስጠት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በዚህም በሁሉም ክልሎች ያሉ የተመረጡ ተማሪዎች በኦንላይን ፈተናቸውን የሚወስዱ ሲሆን ፥ ቀሪዎቹ ደግሞ በተለመደው አግባብ ፈተናቸውን ይወስዳሉም ብለዋል።

የሀገር አቀፍ ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር (ዶ/ር) እሸቱ ከበደ በበኩላቸው እንዳሉት ፥ ፈተናውን በኦን ላይን ለመሥጠት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ ነው።

ተማሪዎች የሙከራ ፈተና የሚለቀቅላቸው ሲሆን ፥ ደጋግመው እንዲሞክሩና እንዲለማመዱ ይደረጋልም ብለዋል።

ለዚህም እንዲረዳ የአሰልጣኛች ስልጠና በመሥጠት ተማሪዎች ተደጋጋሚ ስልጠና እንደሚሠጣቸውም ነው የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ።

ከቀጣይ ሣምንት ጀምሮ የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት እንደሚጀምርም በመድረኩ መገለጹን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.