Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንን በይፋ አስጀመሩ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንን በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ይህ ታሪካዊ ክስተት የኢትዮጵያ አዲስ የፈጠራና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ልማት ጅማሮን የሚያበስር ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የኢኮኖሚ ፈጠራን በማራመድ፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ በማብቃትና ዘላቂነትን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ይሆናል ነው ያሉት።

የኢኮኖሚ ፈጠራን በማራመድ ረገድ ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ የማዕዘን ድንጋይ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ የወጪ ንግድ በማስፋፋትና ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት እንዲሁም የላቁ የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪዎችን በማጎልበት ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እንዲኖረው ታስቦ የተነደፈ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ስትራቴጅካዊ ትኩረቱን በላቁ የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂና በዘላቂ አሠራሮች ላይ በማድረግ፣ ዞኑ ለመላው አፍሪካ የኢኮኖሚ ዞኖች አዲስ ደረጃ ያስቀምጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

መሠረቱን የመንግስት ርዕይ 2025 ያደረገው ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን፣ ከኢኮኖሚያዊ ፕሮጀክትነቱም ባለፈ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም መከበር ያለንን ቁርጠኝነት የሚወክል ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የአካባቢውን ማህበረሰብ በማብቃት ረገድ ኢኒሼቲቩ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሥራዎችን ይፈጥራል፤ የሀገር ውስጥ የስራና የክህሎት እድገትን ያፋጥናል፤ የተጓዳኝ ኢንዱስትሪዎችን እድገት ያበረታታል ፤ በውጤቱም ክልላዊ ልማታችንን ያፋጥናል ብለዋል፡፡

“ለዘላቂነት ቁርጠኛ የሆነው ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን፣ የአካባቢን ተፅእኖ መቀነስ የሚያስችሉ አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎችንና ፈጠራዊ አሰራሮችን በማዋሃድ ለወዳጀ-ከባቢ የኢንዱስትሪ ልማት አዲስ ፈር መቅደድ ይፈልጋል” ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፡፡

በዚህ የለውጥ ፕሮጀክት ሁሉም ኢትዮጵያውያንና ዓለም አቀፍ አጋሮች በድጋፍና በተሳትፎ በመቀላቀል የታሪካዊው ጉዞ አካል እንዲሆኑም ጠይቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.