Fana: At a Speed of Life!

ጊዜው የሚጠይቀውን መስዋዕት ሁሉ ከፍለን የራሳችንን ታሪክ ልንፅፍ ይገባል – ምክር ቤቱ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የወረስነውን ታሪክ እየተናገርን የምንኖር ብቻ ሳንሆን ጊዜው የሚጠይቀውን መስዋዕት ሁሉ ከፍለን የራሳችንን ታሪክ በደማቁ ልንፅፍ ይገባል ሲል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገነዘበ፡፡

ምክር ቤቱ ለ83ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ ቀን በዓል የእንኳን አደረሣችሁ መልእክት አስተላልፏል፡፡

በመልዕክቱም፤ ትናንት እናት አባቶቻችን ጊዜው የሚጠይቀውን ውድ የሆነውን የሕይወት መሥዋዕትነት በመክፈል ጭምር የሀገራችንን ነፃነትና የግዛት አንድነቷን አስጠብቀው በክብር አስረክበውናል ብሏል፡፡

የዛሬው ትውልድ ከአያት አባቶቻችን የወረስነውን ታሪክ እየተናገርን የምንኖር ብቻ ሳንሆን የራሳችንን ታሪክ በደማቁ ልንፅፍ ይገባል ሲል ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ከድህነትና ኋላቀርነት ተላቃ የዜጎችን ብልፅግና ለማረጋገጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተሰማራበት የሥራ መስክ ጠንክሮ በመስራት የራሱን አሻራ በማስቀመጥ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፏል።

የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

እንኳን ለ83ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ ቀን በዓል አደረሣችሁ! አደረሠን!
የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤

የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግንነት በታሪክ የታወቀ ነው፤

ኢትዮጵያ ከብዙ ሺህ ዓመታት በላይ ነፃነቷን አስጠብቃ ታፍራና ተከብራ የቆየች ሀገር ናት፡፡ በተደጋጋሚ የተቃጣባትን የውጭ ወራሪ ኃይል ውድ ልጆቿ በከፈሉት ሁለንተናዊ መስዋዕትነት መክታ በመመለስ ነፃነቷንና የግዛት አንድነቷን አፅንታ መቀጠል ችላለች፡፡

ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያን የቅኝ ግዛቷ ለማድረግ ያልተቋረጠ ምኞት የነበራት አውሮፓዊቷ ሀገር ጣሊያን በአድዋ ጦርነት (1888 ዓ.ም) እናት አባቶቻችን ከአራቱም አቅጣጫ ተጠራርተውና ተሰባስበው ባደረጉት ብርቱ ተጋድሎ፤ በከፈሉት የደምና የአጥንት ውድ የሕይወት መስዋዕትነት ሊከሽፍ ችሏል፡፡

ሆኖም ከአድዋ ድል ከ40 ዓመት በኋላ ፋሺስቱ የጣሊያን መንግሥት ሰፊ የጦርነት ዝግጅት በማድረግ ጣሊያን በዓድዋ ጦርነት የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀልና ኢትዮጵያን በኃይል ወረራ ይዞ የቅኝ ግዛቱ አካል ለማድረግ ዳግም በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያ ላይ የኃይል ወረራ ፈፅሟል፡፡

በዘመኑ ምዕራቡ ዓለም የደረሱበት ስልጣኔ ውጤት የሆኑ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች እና በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለውን የመርዝ ጋዝ በመጠቀም ጭምር የኢትዮጵያን ሕዝብ አዋርዶና አንበርክኮ ነፃነታቸውን ለመውሰድ የሚችለውን ሁሉ የጭካኔና የአረመኔነት ድርጊት ፈፅሟል፡፡

ለአብነት በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በአዲስ አበባ ብቻ በአንድ ጀንበር 30 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በአካፋና ዶማ፣ በምሳርና መዶሻ፣ በሳንጃ፣ በድንጋይና በዱላ ተደብድበውና ተወግረው ጭካኔ በተሞላበት ድርጊት ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡

ከሕፃናት ልጆቻቸው ጋር ሆነው በርካቶች እንዲያልቁም ምክንያት ሆኗል። በአምስት ዓመቱ የፋሺስት ጣሊያን የወረራ ዘመን ቅኝ ተገዥነትን አምርረው የጠሉ ለሀገር ፍቅር ሲሉ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እናት አባት አርበኞች ከአራቱም አቅጣጫ ተጠራርተው ተሰባስበውና ተማምለው ዱር ቤቴ በማለት በዱር በገደሉ፤ በየተራራውና በየኮረብታው ሸንተረሩ እየተዘዋወሩ ለማናቸውም መከራና ስቃይ ሳይበገሩ ጠላትን መግቢያና መውጫ በማሳጣትና በማስጨነቅ ትግላቸው ከወቅቱ ንጉሥ የዲፕሎማሲው ትግል ጋር ተቀናጅቶ ባስመዘገበው ውጤት ወራሪው ጠላት ድል ሆኖና አፍሮ ከሀገር ሊባረር ችሏል፡፡

ስለሆነም ኢትዮጵያውያን አርበኞች እናት አባቶቻችን ውድ የሆነውን የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ነፃነቷና የግዛት አንድነቷ የተጠበቀ የታፈረችና የተከበረች ነፃ ሀገር አስጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድና ለዛሬዎቹ እኛ በክብር ማስተላለፍ ችለዋል፡፡

የተከበራችሁ ውድ ኢትዮጵያውያን !
የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግንነት በሁሉ ዘመናት በታሪክ የሚታወቅ ነው፡፡ ታዲያ በማይጨው ጦርነት ፋሺስት ጣሊያን ከጠረፍ ተነስቶ ወደ ማዕከላዊ ግዛት ሊገባና ለጥቃት ተጋለጥን በዘመኑ የነበረው ዓለም ከደረሰበት ሥልጣኔ ደረጃ እኩል መራመድ ባለመቻላችንና በእኛ ላይ ያስከተለው የዘመናዊ ወታደራዊ ዝግጅት ውስንነት በመኖሩ፣ በወቅቱ ከውጭ የጦር መሣሪያ ለማስገባት የባህር በር ባለቤት አለመሆናችን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና በሌሎች ኃይሎች መያዙ እና ድህነት፣ ኋላቀርነት እና ያሳለፍነው የረጅም ዘመናት የእርስ በርስ ጦርነት ፈተናዎች ተደቅነውብን ስለነበረ ነው።

ነገር ግን ትናንት እናት አባቶቻችን ጊዜው የሚጠይቀውን ውድ የሆነውን የሕይወት መሥዋዕትነት በመክፈል ጭምር የሀገራችንን ነፃነትና የግዛት አንድነቷን አስጠብቀው በክብር አስረክበውናል፡፡ እኛ የዛሬው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ከአያት አባቶቻችን የወረስነውን ታሪክ እየተናገርን የምንኖር ብቻም ሳንሆን ጊዜው የሚጠይቀውን መስዋዕት ሁሉ ከፍለን የራሳችንን ታሪክ በደማቁ ልንፅፍ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ ከድህነትና ኋላቀርነት ተላቃ የዜጎችን ብልፅግና ለመረጋገጥ ሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ በተሰማራበት የሥራ መስክ ጠንክሮ በመስራት የራሱን አሻራ በማስቀመጥ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡

ድህነትና ኋላቀርነትን ልንፀየፍና በአንድነት ተረባርበን ልናጠፋቸው ይገባል፡፡ ሀገር የምትለወጠውና የምትሰለጥነው ለሣይንስና ቴክኖሎጂ ለፈጠራ ሥራዎች ትኩረት የሚሰጥ፤ ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚችል ትውልድ ማፍራት ስትችል ነው፡፡

ይህን እንደ ሀገር እውን ለማድረግ በመዲናችን አዲስ አበባ ጨምሮ በበርካታ ሥፍራዎች ለሣይንስና ቴክኖሎጂ እና ለቱሪዝም ዕድገት ትኩረት የሰጡ ሥራዎች እየለሙና ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡

መንግሥት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል እየሰራቸው ባሉ ደሃ ተኮር የልማት ሥራዎችና የሀገር በቀል ኢኮኖሚው ዘርፍ (ቱሪዝም፣ ግብርና፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ማዕድንና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት) የፕሮግራምና ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ሀገራችን ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት ለማሳካት በትኩረት እየተሰራባቸው ይገኛል፡፡

በመጨረሻም ብሔራዊ አንድነታችንና ሕብረብሔራዊ ወንድማማችነትን እህትማማችነት የሚፈታተኑ ከፋፋይ ትርክቶችን አምርረን በመታገልና በማክሰም፤ ይልቁኑም አሰባሳቢ የሆኑ ትርክቶችን የሚያጠናክሩ ዕሳቤዎችንና ተግባራትን በሰለጠነ የፖለቲካ ባህል በማራመድ፤ የሀገራችንን አንድነት ልናፀናና ለብሔራዊ ጥቅም መከበር መላው ኢትዮጵያውያን ሁላችንም በሀገር ፍቅር ስሜት ተቃኝተን በጋራ እንድንቆም ምክር ቤቱ በዚህ አጋጣሚ መልዕክት ለማስተላለፍ ይወዳል፡፡

በድጋሚ እንኳን ለ83ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ ቀን በዓል አደረሣችሁ! አደረሠን!
ዘላለማዊ ክብር ለእናት አባት ኢትዮጵያውያን አርበኞች!
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤
ሚያዚያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.